የትህነግ ባልበላውም ጭሬ ልድፋው ሴራ ባስቸኳይ ይገታ::

የወልቃይትን ህዝብ የማፈናቀልና የማሳደድ እኩይ ተግባር ባስቸኳይ ይቁም!!

(ልሳነ ግፉዓን ድርጅት የትህነግ/ወያኔ “ባልበላውም ጭሬ ልድፋው” ሴራ ባስቸኳይ ይገታ!!

 

በሃገራችን ኢትዮጵያ የተጀመረውን የሰላምና የአንድነት ጉዞ በመደገፍ ለለውጡም መሳካት የበኩላችን አስተዋፅኦ ለማበርከት ይቻል ዘንድ ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን ከሰላም ወዳዱ ህዝባችን ጋር በመሆን ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎችን ወስዷል: በመውሰድም ላይ ይገኛል።

በተለይም ዛሬ ሃገራችን ኢትዮጵያ የተያያዘቸው ተስፋ ሰጪ የለውጥ ጅማሮ በተግባር መሬት ላይ ወርዶና የሰላምና የዲሞክራሲ ፍሬ አፍርቶ ለዘመናት በትህነግ/ወያኔ መራሹ ዘረኛ ቡድን የዘር ማፅዳት ወንጀል ሲፈጸምበት የነበረው የወልቃይት የጠገዴና ጠለምት ማህበረሰብ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እኩል ፍትህና እርትእ እንዲያገኝ፣ አማራዊ ማንነቱ እንዲከበርለትና፣ ልጆቹን በቀዬው በሰላም ወልዶ እንዲያሳድግና፣ ያለምንም ስጋት በሃገሩ ላይ በሰላምና በነፃነት እንዲኖር የሚያስችሉትን መሰረታዊ የዜግነት መብቶችና ጥበቃዎች እንዲሟሉለት ለማስቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት በመስራት ላይ እንገኛለን።

ይሁን እንጂ መቃብር ሳጥን ውስጥ ሆኖ የሚንፈራገጠው የትህነግ/ወያኔ ዘረኛና ጨካኝ ቡድን የተጀመረው አገር አቀፍ የሰላምና የአንድነት መንገድ እንዲደናቀፍና ህዝባችን ወደ ማያባራ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ እንዲገባ በማለም ከጅምሩ በተለያየ ሁኔታና መጠን በየአቅጣጫው የተለያዩ ትንኮሳዎችንና የሽብር ተግባራትን በህዝባችን ላይ በመፈጸም የሚገኝ ሲሆን፤
የዚህ እኩይ ሴራው ተቀፅላና የመጨረሻ የሽብር ካርድ አድርጎ ሊጠቀምባትና ህዝብን ከህዝብ ጋር ለማጋጨትና ለውጡን ለማደናቀፍ ይረዱኛል በማለት ሌት ከቀን ችግር ከሚፈጥርባቸው አካባቢዎች አንዱና ዋነኛው የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ማህበረሰብ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው። ምክንያቱ ዛሬ በአንድ በኩል የትህነግ/ወያኔ “የትግራይ ሪፐብሊክ” ምስረታ ህልምና ህልውና በሌላ በኩል ደገሞ የመላው የጎንደር፣ የአማራ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ብሎም የዓለም ሰላምና ፍትህ ወዳድ ህዝብ አይንና አትኩሮት በዚያ አለና ነው።

ስለሆነም በታላቁ የመስቀል በዓል እለት ትክክለኛውንና ህዝባችን የሚፈልገውን የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዛችሁ ለምን ወጣችሁ በሚል የትህነግ/ወያኔ አሸባሪና አፋኝ ቡድን በከፈተው ህዝብን የማሸበርና የማዋከብ ወረራ ከመስከረም 17, 2011 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰላማዊ ዜጎች ለአፈና እና ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች የተከፈተባቸውን የጅምላ አፈሳና እስር በመሸሸት በአማራ ክልል ስር ወደ ምትገኘው የሰሮቃ ወረዳ ለመፈናቀል ተገደዋል።
ታላላቅ ሃይማኖታዊ በዓላትን እንኳ በሰላም በቀዬው ከቤተሰቦቹ ጋር ለማክበር ያልታደለው ወገናችን በባንዴራ ሰበብ በአለፉት 5 ቀናት የትህነግ አፋኝ ቡድን በየአቅጣጫው ካፈናቀላቸው ሰላማዊ ዜጎች በተጨማሪ በዳንሻ፣ ድርኩታን፣ አደባይ፣ ወዘተ … የሚኖሩ አማራ ነን ባሉ ወገኖቻችን ላይ “አማራ ነን ካላችሁ ከትግራይ ክልል ውጡና ወደ አማራ ክልል ሂዱ” በማለት ተጨማሪ ሰላማዊ ዜጎችን በሃይል በማፈናቀል ላይ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ችለናል።

እነዚህ ወገኖች ምንም እንኳ በአርማጭሆና በጠገዴ ህዝብ ያላሰለሰ ጥረት ግዚያዊ የምግብና የመጠለያ ድጋፍ ሲያገኙ የቆዩ ቢሆንም፣ አሁን የገጠማቸው የምግብ እጥረት፣ የአልባሳት ችግር፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ እጦትና ለተለያዩ በሽታዎች የመጋለጣቸው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና አስፈሪ በመሆኑ በአፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠው ተፈናቃዮቹ እጅግ ለከፋና ለተወሳሰበ የጤና እና የስነ ልቦና ችግር የሚጋለጡ መሆኑ ግልጽ ነው።
ሰለሆነም መንግስትና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከልሳነ ግፉዓንና ከተፈናቃይ ወገኖቻችን ጎን በመቆም ለተጋረጠበን ትህነግ/ወያኔ ሰራሽ ሴራ ተገቢውን ትኩረት በመስጠትና ችግሩንም በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ እልባት ለመስጠት እያደረግን ባለነው ጥረት ላይ ወገናዊ ድጋፋችሁን በመስጠት የሚከተሉትን የመፍትሄ እርምጃዎች ጋራ እንድንወስድ በትህትና እንጠይቃለን።

1ኛ. ቀን በቀን እየጨመረ የመጣውን የተፈናቃዮች ቁጥር በአቸኳይ ለመግታት የፌደራሉ መንግስትና የአማራ ክልላዊ መንግስት ጣልቃ በመግባት በትግራይ ክልል ስር የሚገኙ የአማራ ተወላጆችን ደህንነትና ሰላም እንዲያስጠብቅ፣
2ኛ. ከመስቀል በዓለ ጋር በተያያዘ ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙት የወልቃይት ተወላጆች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣
3ኛ. ተፈናቃዮቹ የሚያስፈልጋቸው የምግብ፣ የመጠጥና፣ የአልባሳትና፣ የመድሃኒት አቅርቦት በአስቸኳይ እንዲሟላላቸው፣
4ኛ. የፌደራሉ መንግስትና የአማራ ክልላዊ መንግስት ለተፈናቃዮቹ ቀጣይ ደህንነት ሙሉ ዋስት በመስጠት፣ አስፈላጊውን ጥበቃና ከለላ በማድረግ ወደ ቀደመ ቀያቸው በመመለስ የመልሶ ማቋቋም ስራ በአፋጣኝ እንዲሰራ፣
5ኛ. ህዝባችን በትህነግ/ወያኔ የሚደርስበትን የዘር ማፅዳትና ማጥፋት ወንጀል በዘላቂነት ለማስቆምና ህዝባችን ፍትህና ሰላም ያገኝ ዘንድ የፌደራሉ መንግስትና የአማራ ክልላዊ መንግስት ለህዝባችን የተራዘመ የአማራ ማንነት ጥያቄ አፋጣኝ መልስ ይሰጡ ዘንድ በትህትና እንጠይቃለ።

ሰላማችንና አንድነታችን በትግላችን እናረጋግጣለን!!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!

ልሳነ ግፉዓን ድርጅት
መስከረም 22, 2011 ዓ.ም