ረቂቅ /Abstract/
ኢትዮጵያ ሉዓላዊትና ህልውናዋ የተጠበቀ ታላቅ ሃገር ከማድረግ ጀምሮ እስከ ዛሬዋ እለት ድረስ ኢትዮጵያዊው ሁሉ በሚያደርገው የነፃነትና የፍትህ ትግል ውስጥ የጎንደር ህዝብ ያበረከተውና እያበረከተ የሚገኘው አስተዋፅኦ እጅግ ከፍተኛና ወሳኝ ትርጉም ያለው እንደሆነ የታሪክ መዛግብት የሚያረጋግጡትና እኛው ዛሬ በዘመናችን እየኖርበት የምንገኘው እውነት ነው።
ስለሆነም ኢትዮጵያንና ህዝቧን የሚጠሉና ሊያጠፏት ዘወትር ጉድጓድ የሚቆፍሩላት የውጭ ጠላቶቿ፣ እንዲሁም ከማህጸኗ የወጡ አምባገነን፣ ሙሰኛ፣ ጎጠኛና፣ ባንዳ ልጆቿ በሄዱና በመጡ ቁጥር ዋነኛ የጥቃት ኢላማቸው ከሚያደርጓቸውና ሊያንበረክኳቸው ከሚዘመትባቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች መካከል ጎንደርና ህዝቧ ቅድሚያውን የሚይዙት። ለዚህም ነው የእናት ሃገሩን ዳር ድንበር በንቃትና በፍጹም ጀግንነት አስከብሮ የሚኖረው ህዝባችን ለተደጋጋሚ የወራሪዎችና የተስፋፊዎች ተቀዳሚ ሰለባ ሲሆን የምናገኘው።
በተለይም የጎንደር ታሪካዊና ለም መሬቶች የሆኑት አርማጭሆ፣ መተማ፣ አብደራፊ፣ ሁመራ፣ ወልቃይት፣ ጠገዴና፣ ጠለምት ከጎረቤት ሃገሮች የሚመጣውን ማንኛውንም ወረራና ጥቃት በመመከትና ብሎም በመቀልበስ የከፈሉት መስዋዕትነትና ያሳዩት ጀግንነት ዛሬም ድረስ በሃገራችን ታሪክ ውስጥ ደምቀው የሚታዩ ሲሆን፤ በጠላቶቻችን የሽንፈት መዝገበ ቃላት ዝርዝር ውስጥ ከሰፈሩትና ጥርስ ከተነከሰባቸው መካከል እኒህ ጎንደሬዎች ዋነኞቹ የመሆናቸው ጉዳይ ሳይታለም የተፈታ ነው።
ታዲያ እነዚህ ቀደምት ጠላቶቻችን በተደጋጋሚ ሊያጠቁን ሞክረው የሚመኩበት ውጤት ካስመዘገቡላቸው ጥቂት ጥቃቶች መካከል በዋናነት ሊመዘገብ የሚችለው በባንዳዎቹ የሻዕቢያና የህወሃት ጥምረት የተከፈተብን ሃገራዊ ወረራና ጥቃት አንዱ ነው። ይህም የተቀናጀ ጥቃትና ወረራ ባንዳዎቹን ኤርትራን እንዲገነጥሉና አስገንጣዮችንም ለአለፉት 27 ዓመታት በምኒልክ ቤተ መንግስት እንዲፈነጩና አንድን ታላቅ ህዝብ በጎሳ ሸንሽነውና አሳንሰው እርስ በእርስ የጎሪጥ እንዲተያይ ለማደረግ ያስቸለ ሲሆን የ40 ዓመት ጉዞውም በሚሊዩን የሚቆጠሩ ውድ ወገኖቻችን ህይወት እንዲጠፋና አካላቸው እንዲጎል አድርጓል።