ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ስብዕና በቤተሰብ እይታ (በአብዩ በለው)

ግንቦት 4 ቀን 2010 ዓ ም

ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ስብዕና በቤተሰብ እይታ (በአብዩ በለው)

ዛሬ በጀርመን የኢትዮጵያውያን የውይይትና የትብብር መድረክ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ የተሰዉበትን 150ኛ ዓመት ለመዘከር በተዘጋጀው ታሪካዊ ዝግጅት ላይ ለመታደም የተገኛችሁ

– ክቡራን የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች፣

– የተከበሩት አንጋፋ ጋዜጠኛና ደራሲ ክቡር አቶ ተክሌ የኋላ፣

– የተከበርከው የአንድነት፣ የፍትህና፣ የዲሞክራሲ ታጋይና የሰላማዊ ትግል አርበኛ ክቡር አቶ አንዷለም አራጌ፣

– የተከበራችሁ የዚህ ታላቅ ዝግጅት አዘጋጆችና አስተባባሪዎች፣

– እንዲሁም እኛን እንግዶቻችሁንና ጠሪዎቻችሁን አክብራችሁ ከቅርብም ሆነ ከሩቅ የተሰባሰባችሁ ክቡራንና ክቡራት ወገኖቼ

በቅድሚያ በዚህ በጀርመን ሃገርና አካባቢዋ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፈር-ቀዳጅ፣ የአንድነትና የስልጣኔ አባትና፣ ባለ ራዕዩ ንጉሰ ነገስት የተሰዉበትን 150ኛ ዓመት ለመዘከር ይህን የመሰለ ታላቅና ታሪካዊ ዝግጅት በማዘጋጀታችሁ እንደ አንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ የተሰማኝን ልባዊ ደስታና ሃሴት እየገለፅኩ፤ ይልቁንም እኔ እንደ አንድ ቤተሰብ በዚህ ዝግጅት ላይ እንድታደም የክብር እድሉን ስለሰጣችሁኝ በእጅጉ አመሰግናለሁ።

ክቡራትና ክቡራን ወገኖቼ!

ዛሬ እዚህ መድረክ ላይ ከእናንተ መካከል ተገኝቼ አጭር መልዕክት እንዳቀርብና እንድወያይ እድሉ/ግብዣው ከቀረበልኝ እለት ጀምሮ ከሚሰማኝ ታላቅ ደስታ ባልተናነሰ መጠን እጅግ ያሳሰበኝ ነገር ቢኖር እናንተ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ፊት ምን ይዠ እቀርባለሁ? የሚለው ሃሳብ ነበር። ምክንያቱም፦

1ኛ. ስለ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ያልተነገረ፣ ያለተፃፈና፣ ያልተዘፈነ ምን የተለየ ነገር ላቅርብ? የሚለው ሲሆን፣

2ኛ. የእኔ ውልደት ከንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ የዘር ሃረግ ውስጥ በመሆኑ ምክንያት በቤተሰብ ውስጥ ስለ ንጉሰ ነገስቱ የምሰማቸውና የማገኛቸው ታሪኮችም ሆኑ ሃሳቦች እኛን በማነፅና የትውልድ አደራ እንድንሸከም ማዘጋጀት ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው የትኛውን አደባባይ እንደሚወጣና ለዚህ መድረክ እንደሚስማማና እንደሚመጥን ሳወጣና ሳወርድ ነው።

ስለሆነም ዛሬ ስለ አባታችንና ንጉሰ ነገስታችን በብዙው ከቤተሰብ፣ በመጠኑ ደግሞ ከመፃህፍትና ከተለያዩ ምንጮች የተማርኩትንና የተረዳኋቸውን ቁምነገሮች በአጭሩ “ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ስብዕና በቤተሰብ እይታ” በሚል ርዕስ ይህቺን ፅሁፍ አዘጋጅቼ አቅርቢያለሁና በትዕግስትና በማስተዋል ታዳምጡኝ ዘንድ በታላቅ አክብሮትና ትህትና እጠይቃለሁ።

ውድ የዚህ ጉባኤ ታዳሚዎች!

ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ከራሳቸውና ከቤተሰቦቻቸው በላይ ለሃገራቸውና ለወገናቸው የነበራቸውን እውነተኛ ፍቅርና የታላቅነት ራዕይ በእራሳቸው መሰዋዕትነት አትመውት በክብር አልፈዋል። ይህ ዘመን ተሻጋሪ ራዕያቸውና አኩሪ ገድላቸው በጠላት ሴራና በተለያዩ ምክንያቶች ተቀብሮ እንዳይቀርና ከትውልድ ትውልድ በክብር እንዲተላለፍ ብዙ ተደክሞበታል ብዙ ወገኖች ያለመታከት ታግለውለታል። ከዚህ ትግል መካከል ይህ ዛሬ ንጉሰ ነገስቱ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ ክብር ሲሉ እራሳቸውን የሰዉበት 150ኛ ዓመት ዝግጅት አንዱ ነው። ታዲያ ይህ ታላቅና ታሪካዊ መድረክ ያጎናጸፈኝን እድል ተጠቅሜ በእናንተ በወገኖቼ ፊት ላመሰግናቸውና ላወድሳቸው የምፈልጋቸው የታሪክና የእውነት ባለውለታዎች አሉኝና በቅድሚያ እነሱን እንዳመሰግናቸው ይፈቀድልኝ ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

1. ያለማንም ጎትጓች፣ ያለማንም አስገዳጅነትና፣ ያለምንም ድርጎ/ክፍያ፣ ወይም ያለቁሳዊ ትርፍ የንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ከያለበት እየፈለጉና እያስፈለጉ፣ በብዙ መስዋዕትነትና ውጣውረድ ለትውልዱ በሚገባውና በሚረዳው መልኩ እያዘጋጁ ያስተላለፉ የታሪክ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ደራሲያን፣ ሙዚቀኞች፣ ሰዓሊያንና፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣… ወዘተ በሙሉ ላደረጉት ታላቅ አስተዋፅኦና ለከፈሉት መስዋዕትነት ሁሉ በእራሴና በቤተሰቦቼ ስም ላመሰግናቸው እወዳለሁ።

2. የኢትዮጵያ ህዝብ በእውነት የተዋለለትንም ይሁን የተዋለበትን ውለታ አዋቂ፣ የማይረሳና፣ ጊዜውንም ጠብቆ ብድር ከፋይ እንደሆነ እሰማለሁ። በተግባርም አይቻለሁ። ወደ ፊትም ይህ ሂደት የሚቀጥል ይመስለኛል። ከእነዚህ የህዝብን ታሪክና ትውፊት ከትውልድ ወደ ትውልድ የማስተላለፊያ ይትባህሎቻችን መካከል አንደኛውና ዋነኛው ዘዴ የመጠሪያ ስሞችን መጠቀም ይመስለኛል። ታዲያ የንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ከዘመንና ከተፅዕኖ ብዛት እንዳይረሳና ተቀብሮ እንዳይቀር ያደረገው እስከዛሬ ድረስ ከሰሜን ኤርትራ በረሃ እስከ ሞያሌ ጫፍ፣ ከአፋር ሸለቆ እስከ ቋራ ጫካ ድረስ ልጆቻቸውን “ቴዎድሮስ” ብለው የሚጠሩ እልፍ አዕላፍት ወላጆች መኖራቸው ነው። እናም እነዚህ በዘመናት ውስጥ ያለፉና የሚያልፉ የእልፍ “ቴዎድሮሶች” ወላጆች የአባታችንና የንጉሰ ነገስታችን ታሪክ ከልጆቻቸው ስም ጋር ህያው ሆኖ እንዲቀጥል በማድረጋችሁ እንደ አንድ ቤተሰብ ላመሰግናችሁ እውወዳለሁ።

ውድ የሃገሬ ልጆች!

ዛሬ ከ 150 ዓመታት በኋላ የምናስባት አርብ ሚያዝያ 6 1868 ዓ.ም

የመቅደላ አምባ ለንጉሰ ነገስት አፄ ቴዎድሮስ እንደ ክርስቶስ የማያልፏትን መራራ ፅዋ የተጎነጩባት እንደ ቀራንዮ ያለች ተራራማ ቦታ ስትሆን፣ እለቷም እንደ እውነተኛዋ የክርስቶስ የስቅለቱ እለት “እለተ አርብ” ያለች በወራሪው የእንግሊዝ ጭሳማ መድፎች ጥቁር ጭስ ኢትዮጵያ ንጹህ ሰማይ የጨለመበት እለት ነበር።

ይህቺ ቀንና ቦታ ለህፃኑ ቅድመ አያቴ ለልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስና ለንግስቲቱ ለዕቴጌ ጥሩወርቅ እንደ ቅድስት ድንግል ማርያምና አንደ ሃዋርያው ዩሃንስ በብዙ መከራና ድካም እስከ መስቀሉ ስር ተጉዘው በምድር ላይ የሚያፈቅሩትንና የሚመኩበትን ብቸኛ ሰው ጭንቀት፣ ስቃይ፣ መከራና፣ በመጨረሻም ሞቱን በአይናቸው ያዩበት ቀንና ቦታ ነች።

ዛሬ እኔ እንደ አንድ ክርስቲያን ከ 2010 ዓመታት በፊት የተፈፀመው የፈጣሪዬ የክርስቶስ የስጋ ህማሙና ሞቱ በእጅጉ እንደሚያሳዝነኝና እንደሚያመኝ ሁሉ፤ የንጉሰ ነገስቱ ህማማቸውና ሞታቸው ዘወትር ባሰብኩት ቁጥር እንዲሁ በእጅጉ ያሳዝነኛል። ያመኛል።

የክርስቶስ ሞቱ ለጨካኞችና ለሃሰተኞች የአይሁድ መሪዎችና ተባባሪዎቻቸው የተሸበሩበት፣ የተዋረዱበትና፣ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ የሚከተላቸው በደል ሲሆን፣ የንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ሞታቸው እንዲሁ ለወራሪው የእንግሊዝ መንግስትና ለተባባሪዎቻቸው ታሪካቸውን በወራሪነት ጥቁር መዝገብ ያሰፈሩበትና፣ ዘመናቸውን ሁሉ የሚያሳድዳቸው የኢትዮጵያውያን ሁሉ በደል ሆኖ አልፏል።

ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው፣

ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በእጃቸው፣

ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው። ተብሎ ተጽፏልና ነው።

ይሁን እንጂ የክርስቶስ ሞቱ ለእኛ ለምናምን ክርስቲያኖች የጠላታችን ድል መንሻ፣ የሃጢያታችን መደምሰሻ መስቀለ-ክርስቶስ እንደሆነልን ሁሉ፤ የንጉሰ ነገስቱ ሞት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የሉዓላዊነታችን ማስከበሪያና የአንድነታችን ማሰሪያ ፅኑ ቃልኪዳን ሆኖልናል። ይህቺ እለትና የመቅደላ አምባ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ከጨለማው የመሳፍንት ዘመን ውድቀታችን ዳግም በአንድነት ህይወትን ዘርተን በሉዓላዊነት የተነሳንበትና ኢትዮጵያዊነትን ከነሙሉ ክብሩና ኩራቱ የወረስንበት ታሪካዊ እለታችንና አምባችን ናቸው።

ወጣቱ ከያኒ

አምጡ ቆርጣችሁ ከሹሩባው ላይ፣

ኪዳን እንሰር እንዳንለያይ። እንዳለው ማለት ነው።

የተከበራችሁ ወገኖቼ!

ዛሬ በተሰጠኝ ታላቅ እድልና ክብር ተጠቅሜ ስለ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ እንደ አንድ የቤተሰባቸው አባል ምን አይነት እይታ እንዳለኝ በሶስት አጫጭር ጉዳዮች ላይ ለመናገር እወዳለሁ።

1. ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ የፍቅርና የደግነት አባትነት

ንጉሰ ነገስት ዓፄ ቴዎድሮስ ከተሰዉ እነሆ 150 ዓመታት ተቆጠሩ። ምንም እንኳ ጊዜው እረጅም በመሆኑ ምክንያት አብዛኛው የቅርብ ትውልድ ቢያልፉም ቀላል የማይባሉ ታሪኮች በተዋረድ እኔ ትውልድ መድረሳቸው አልቀረም። በተለይም ደግነታቸውንና አባታዊ ፍቅራቸውን በሚመለከት በብዙ እየሰማሁ አድጊያለሁ።

ህፃናትን ማፍቀራቸው፣ ለታዳጊዎች ሰፊ ጊዜና ተገቢውን አትኩሮት ሰጥቶ የማሳደግና የመንከባከብ ባህሪያቸው እጅግ የተለየ እንደ ነበር ሁሌም በፍቅር የምንሰማው ታሪካቸው ነው። በተለይም ከአድካሚውና ከአስጨናቂው ሃገር የማቅናትና አንድ የማድረግ ተቀዳሚ ተልኳቸው ጥቂት ፋታ ሲያገኙና ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ተቀዳሚው ስራቸው ከልጆች ጋር መጫወትና አሽተተው የማይጠግቡትን የልጆች ውብ ጠረን ማጣጣም ይወዱ ነበር ይባላል።

አልፎ አልፎም ቢሆን ይህ ከልጆች ጋር የመሆን ፍቅራቸው እየጠናባቸው ሲያስቸግራቸው ይሄድና ከውስብስቡ ሃገራዊ ስራቸው መሃል ጣልቃ እየገባ ሲረብሻቸው ይታያል። ምንም እንኳ ነጮቹ የሰው ሃገር ወረውና ሊመዘብሩ ዘምተው አልሳካላቸው ሲል ስም ማጥፋትና መሳደብ የዘወትር ተግባራቸው ቢሆንም እነዚህን እውነታዎች አልፎ አልፎም ቢሆን በአንዳንድ የውጭ ሃገር ሰዎች መጽሃፎች ላይ በመገረምና በአድናቆት መልክ ጽፈዋቸው እናያለን።

እዚህ ላይ ለዚህ ጉባኤ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ አንድ ገጠመኝ ላንሳና ልለፍ።

ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ልጆችን ሲስሙ አንገታቸው ስር ገብተው ነው ይባላል። መሳም ብቻ ሳይሆን የልጆች የአንገት ጠረን በደንብ ማሽተት ይወዱ ነበር ይባላል። ታዲያ ከእለታት በአንድ ቀን ከወዳጆቻቸው ጋር ሲጫወቱ ሁሌ እንደ ሚያደርጉት ጥያቄ ይጠይቃሉ። ጥያቄውም በዓለም ላይ ጣፍጭና የምይጠገብ ሽታ የምን ሽታ ነው? የሚል ነበር። በወቅቱም ሁሉም የንጉሰ ነገስቱን ጥያቄ ለመመለስና አድናቆት ለማግኘት በመረባረብ የሚያውቀውን መልካም ሽታ ይናገር ነበር። ነገር ግን መልሱን ያወቀ አልነበረም ይባላል። በዚያን ጊዜ ሁሉም ተስፋ ቆርጠው ጥያቄውን እራሳቸው ንጉሰ ነገስቱ እንዲመልሱ ይጠይቋቸዋል። እርሳቸውም ሲመልሱ ሁሌም የማይሰለችና የማይጠገብ ጣፋጭ ሽታ “የህጻን ልጅ የአንገት ሽታ” ነው አሉ ይባላል።

አውሮጳዎቹ ምንም እንኳን ንጉሰ ነገስት ዓፄ ቴዎድሮስን ፍጹም ጨካኝ አድርገው ለማስተዋወቅ ብዙ ቢደክሙምና በብዙው ብጽፉም ለእነርሱ ህፃናት ልጆች ሳይቀር የነበራቸው ፍቅርና የሳዩት የነበረውን ደግነት መሸሸግ አልተቻላቸውም። ይልቁንም ሃገራችን ኢትዮጵያ በእንግሊዝ ወራሪ ሃይል በተደፈረችበትና ንጉሰ ነገስቱም በጠላት ጦር በተከበቡበት የመጨረሻው ሰዓት እንኳ ይህ አባታዊ ፍቅራቸውና ደግነታቸው እንዳልተለያቸው በመፃህፎቻቸው ላይ በግልጽ አስፍረውት እናያለን።

ይህ ልጆችንና ቤተሰብን የመውደድና የማክበር ባህሪ ሲወርድ ሲዋረድ እኔ አያት ላይ ደርሶ በተደጋጋሚ ሲከሰት እንመለከታለን። አያቴ ደጃዝማች ካሳ መሸሻ ቴዎድሮስ እጅግ በጣም ልጆቻቸውን አፍቃሪና ደግ አባት እንደ ነበሩ አውቃለሁ። እዚህ ላይ ሁሌም የምሰማውን ባህሪያቸው መካከል አንዱን ለማሳያ ያህል ላውሳና ልለፍ።

የደጃዝማች ካሳ ህፃናትን የመውደዳቸው ነገር በቤተሰቡ ዘንድ እንደ ስስ-ብልት/ደካማ ጎን/ ይታወቅና ይቆጠርባቸው ነበር አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ጌቶቹ እጅግ በአመንክዮ የሚያምኑና ግርማ ሞገሳቸው አስፈሪ ነበር ይባላል። ከዚህም በመነሳት አንዳንድ ጊዜ በቤተሰቡ ውስጥ የእርሳቸው ውሳኔና እርዳታ ወይም ሌላ ነገር ሲፈለግና ነገር ግን በወቅቱ እርሳቸው ፊት ቀርቦ ጉዳዩን የሚያስረዳና የሚያሳምን ደፋር ሰው ከሌለ እናቶች ህጻናትን ወደ እርሳቸው ይልኩ ነበር ይባላል። እርሳቸውም ህፃናቱ አድርጉልኝ ያላቸውን ነገር ሳያደርጉና ልጆቻቸውን ሳያስደስቱ ከቤት አይወጡም ይባል ነበር። ይህም ነገር አንዳንዴ ከጌቶቹ ገንዘብ ለመጠየቅ ሲገለገሉበትና ሌላም ጊዜ ከበድ ወዳለው የይቅርታ ማድረግ ጉዳይ ሲጠቀሙበት ይስተዋል ነበር።

2. የንጉሰ ነገስቱ ጥልቅ ባለራዕይና ፅኑ መሪነታቸው

ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያና ለህዝቧ የነበራቸው ራዕይና ይህንም ራዕይ ከግቡ ለማድረስ ይሰጡት የነበረው የመሪነት ሚና በቤተሰቦቻቸው አይን ልዩ ስፍራ አለው።

በግልጽ እንደ ሚታወቀው ንጉሰ ነገስቱ እራሳቸውን የኢትዮጵያ እና የህዝቧ አንጡራ ሃብት አድርገው ይቆጥሩ እንደሆን እንጂ አንድም ጊዜ የቤተሰቦቻቸው ወይም የዘመድ አዝማዶቻቸው አሴት አድርገው አያስቡም። በአፃሩ ደግሞ የኢትዮጵያ ባለቤት ህዝቧ እንዲሆን እንጂ የእርሳቸው ወይም የጓደኞቻቸው ወይም የቤተሰቦቻቸው በግል ንብረትነት እንዳትያዝ አጥብቀው ሰርተዋል። ኢትዮጵያንና ህዝቧን ታላቅ የማድረግ ራዕያቸውን እውን ለማድረግ ሲሰሩ መሰረቱን እንዴት በፅኑ እንደ መሰረቱት ቀጥሎ ለማሳየት እሞክራልሁ።

ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ከሸዋ ዘመቻ በድል ሲመለሱ ታዳጊውን ወጣት ምኒሊክ ሃይለመለኮትን ይዘው ወደ ጎንደር መመለሳቸው ይታወቃል። በምርኮ አይን ካየነው የንጉሰ ነገስቱ ድርጊት ምን አልባትም በዘመኑ የነበረና የተለመደ አሰራር ይሆን ይሆናል። ነገር ግን እርሳቸው በወጣቱ ምኒልክ ላይ ያከናወኑትን ቁምነገሮች ስንመለከት ጉዳዩ ከምርኮኛ ጨዋታ እጅግ የላቀ እንደሆነ እንረዳለን።

እጅግ አድርጌ የማከብራቸው አርበኛ አቶ አስፋው ጀምበሩ አጤ ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያ የተወለዱ ለኢትዮጵያ የተሰዉ ንጉሠ ነገሥት ናቸው” በተባለው መፅሃፍቸው በገጽ 4 ላይ እንዲህ ብለው ፅፈዋል።

“አጤ ቴዎድሮስ በመኳንንትና በመሳፍንት የተከፋፈለች ኢትዮጵያን የአንድ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛት ካደረጉ በኋላ ቤተ መንግሥታቸውን ጎንደር አዘዞ ሎዛ ማርያም አድርገው ስለነበር

1ኛ. አጤ ምኒልክ ሃይለመለኮትን፣

2ኛ. ራስ መሸሻ ቴዎድሮስን የመጀመሪያውን ትልቁን ልጃቸውን፣

3ኛ. ራስ ቢትወደድ መንገሻ አትከምንና

4ኛ. አጤ ዩሃንስን ከሌሎች ለኢትዮጵያ ይጠቅማሉ ከሚሏቸው ወጣቶች ጋር መርጠው በጎንደር አዘዞ ተክለሃይማኖት ሲያስተምሯቸው ከቆዩ በኋላ ቤተ መንግስቱ ከጎንደር አዘዞ ሎዛ ማርያም ወደ ደብረታቦር ሲዛወር እነዚህን ተማሪዎች ዛሬ ለትምህርት ወደ አውሮፓና አሜሪካ እንደሚላከው ወደ ቋራ ማህበረ ሥላሴ ገዳም ተልከው ትምህርታቸውን አጠናቀው እንደተመለሱ በገዳሙ መምህራን በሰጡት የብቃት ማረጋገጫ መሰረት የሚከተለው ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል።” በማለት ጽፈዋል። (የማዕረጉን ክፍል ዘልየዋለሁ)

የተከበራችሁ ወገኖቼ!

ከዚህ የታሪክ እውነታ ውስጥ እኔ እንደ ቤተሰብ ቀልቤን የሚገዛውና የሚመስጠኝ ቁምነገር ቢኖር ንጉሰ ነገስቱ ትላንት በምርኮ ያመጡትን ታዳጊ ወጣት እኩል ከበኩር ልጃቸውና ከሌሎች መሰል ኢትዮጵያዊ ወጣቶች ጋር በእውቀት፣ በማስተዋልና፣ በሞገስ ኮትኩተው አሳድገው ኢትዮጵያንና ህዝቧን በአደራ እንዲረከባቸውና ራዕያቸውን እንዲያስቀጥል የማብቃታቸው ነገር ነው። (ቅድመ አያቴ ወጣቱ መሸሻ ቴዎድሮስ የወጣቱ ምኒልክ የእድሜ እኩያ እንደነበሩ እዚህ ላይ ማስታወስ ያሻል)

ንጉሰ ነገስቱም እራሳቸውን ለውድ ሃገራቸውና ለህዝባቸው ክብር ሲሉ መሰዋታቸውን ተከትሎ ስልጣን ላይ የወጡት አፄ ዩሃንስም ይሁኑ አፄ ምኒሊክ አንድ በአንድ ተግባር ላይ ያዋሉት ከስጋ ወላጆቻቸው የተማሩትንና የወረሱትን የዘመነ መሳፍንት አሰራርና አስተሳሰብ ሳይሆነ ዘመነ መሳፍንትን ቀጥቅጦ ካጠፋው የአንድነት፣ የስልጣኔና፣ የታላቅነት የመንፈስና የተግባር አባታቸው ከሆኑት ከንጉሰ ነገስት ዓፄ ቴዎድሮስ እግር ስር ቁጭ ብለው የተማሩትን ነበር።

ይልቁንም የያኔው ታዳጊ ወጣትና “ምርኮኛ” የነበሩትና በኋላም የታላቋ ኢትዮጵያ መሪ የሆኑት አፄ ምኒሊክ ከአፄ ዩሃንስ የተቀበሏትን ኢትዮጵያን አንድነቷን ጠብቀው፣ ስልጣኔዋን አስፋፍተው፣ ሰላሟን አጽነተውና፣ ወራሪ ጠላቶቿን ድል በመንሳት ከንጉሰ ነገስት ዓፄ ቴዎድሮስ የወረሱትን ራዕይና የተረከቡትን አደራ የላቀ ደረጃ ላይ አድርሰው አልፈዋል።

የተከበራችሁ ወገኖቼ!

በዚህ ሁሉ ጊዜ ቅድመ አያቴ ወጣቱ መሸሻ ቴዎድሮስ የት ነበሩ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። ወጣቱ መሸሻ ከአባቱ በጅምር የተረከባትና አደራዋን ያፀናችበት ኢትዮጵያ አንድነቷ እንዳይፈርስና ተመልሳ ወደ ጨለማው ዘመነ መሳፍንት ስርዓት እንዳትገባ ከኢትዮጵያዊ የመንፈስና የአላማ ወንድሞቹ በቅድሚያ ከአጼ ዩሃንስ በኋላም ከአጼ ምኒልክ ጋር በመሆን የቋራን፣ የእንፍራዝን፣ የደንቢያን፣ ….. ግዛት ይዞ በሰላምና በፍቅር አገር ሲያቀና ነበር። የንጉሰ ነገስት ዓፄ ቴዎድሮስ ልጅ የእራስነት ማዕረግ የተቀበለው ከአጼ ምኒሊክ እጅ ነበር። በዚህም የታሪክ ሂደት ትላንት የነበሩት ቅድመ አያቴም ሆኑ የዛሬው እኔ እንደ አንድ የቤተሰቡ አባል በእጅጉ የምንኮራ ሲሆን፤ የንጉሰ ነገስቱን አስተዋይነት፣ የራዕያቸውን ጥልቀትና ጥራት፣ የመሪነት ብቃትና ለአላማ መሰጠት ለአብራካቸው ክፋይና ለኢትዮጵያውያን የመንፈስ ልጆቻቸው እኩል ያወረሱት ብቸኛና ዘላለማዊ ሃብት መሆኑን ስረዳ ልቤ ሁሌም ሃሴትን ታደርጋለች።

3. የንጉሰ ነገስቱ ኢትዮጵያዊ ቆራጥነትና ሩህሩህነት

የውጭ ሃገር ሰዎች በተለያየ መልኩ ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ሃገራችንን ለመመዝበርና ለመበርበር ጥረት ያደርጋሉ። በተለይም በንጉሰ ነገስቱ ዘመን አንዴ የሃይማኖት ሰባኪ/ቄስ፣ ሌላ ጊዜ ነጋዴ፣ ድብብቆሹ አላዋጣ ሲል ደግሞ የመንግስታት ወኪልና መልዕክተኛ እየሁኑ ወደ ቅድስቲድቱ ሃገራችን እንደ ውሃ ቀጂ ሲመላለሱ ማየት የተለመደ ነበር።

ሁላችሁም እንደምታውቁት ንጉሰ ነገስቱ ለሃገራቸውና ለህዝባቸው ክብርና አንድነት ከማንም በላይ ቀናኢ ነበሩና ይህን የውጭ ሃገር ሰዎች ያለተገባና የብልጣብልጥ አካሄድ በዕጅጉ ይጠራጠሩና ይቃወሙ ነበር። ከዚህም በመነሳት ወደ ሃገራቸው የሚመጡትን የውጭ ሃገር ዜጎች መግቢያ መውጫቸውን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ማስቆም እስኪችሉ ድረስ ከመጡ አይቀር የእጅ ሙያ ያላቸውና ሃገራቸውንና ህዝባቸው ወደ ስልጣኔና እድገት የሚወስዳቸውን ሙያ እንዲያስተምሩላቸው ይጥሩ ነበር። በዚህም ጥረታቸው የዛሬይቱን ዘመናዊት ኢትዮጵያ የእድገትና የስልጣኔ ብርሃን ጭላንጭል ለተተኪዎቻቸው ፈንጥቀው አልፈዋል።

ይሁን እንጂ እነዚህ የውጭ ሃገር ሰዎች ከንጉሰ ነገስቱ ፈቃድና ከሃገራችን ፋላጎት ውጭ ሲንቀሳቀሱና በተደጋጋሚ የመጡበት ሃገር አላማና ተልዕኮ ለማሳካት ሲሽሎከሎኩና ሀገራችን ሲሰልሉ ተይዘዋል። በዚህም የጥፋትና የስለላ ተግባራቸው የእግር ጫማን አራግፎ ከሃገር መባረር እስከ እግር በረት እስር ድረስ ቅጣት ደርሶባቸዋል።

የተከበራችሁ ወገኖቼ!

የሃገሬ ሰው “የከለከሉት ለማኝ ተሳድቦ ይሄዳል” እንዲል እነዚህ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ለመመዝበርና ለመበርበር የመጡ የውጭ ሃገር መንግስታት ወኪሎች ሴራቸው ሲከሽፍና የቋመጡለትን የኢትዮጵያን ቅዱስ አፈር ዳግም እንደ ማይረግጡትና እንደማያገኙት ሲያውቁ ይህን ምድራዊ ገነት የከለከላቸውንና ሴራቸው ያከሸፈባቸውን የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት በመፃህፍቶቻቸውና በጋዜጦቻቸው አብዝተው መሳደብና ስማቸውንም ጥላሸት መቀባት ከዋነኛ ግብራቸው አንዱ ነበር። መኳንንቱንና መሳፍንቱን በጥቅማጥቅም ማባበል፣ መደለልና፣ ማስከዳት እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው።

ከነዚህም ስድቦቻቸውና የስም ማጥፋት ዘመቻዎቻቸው መካከል ግንባር ቀደሞቹ ንጉሰ ነገስቱን ጨካኝና አውሬ አድርጎ ለዓለም ማስተዋወቅ የሚጠቀሱ ናቸው። የኮሶ ሻጭ ልጅነታቸውም እንዲሁ። እነዚህ የውጭ ሃገራት ሰላዮችና መዝባሪዎች በእጅጉ የደበላለቁትና ሊያዛቡት የሞከሩት ኢትዮጵያዊ ቆራጥነትን ከጭካኔ ጋር በማመሳሰል ነው። እውነታውን በፅሞና እና በማስተዋል ለመረመረና በቀዳሚነት የእራሳችንን የመረጃ ምንጮች ለተጠቀመ ማንኛውም ነጻ ሰው ፍንትው ብሎ የሚታየው ነገር ቢኖር የንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ድርጊት ኢትዮጵያዊ ቆራጥነት እንጂ ጫካኝነት አይደለም። ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ፍጹም የሚወዱ እሩሩህና ደግ አባትና መሪ እንጂ እነርሱ እንደሚሉት ጨካኝና ክፉ ሰው አልነበሩም። ኢትዮጵያዊ ቆራጥነትና ጨካኝነት ስራቸውና ትርጉማቸው ለየቅል ነው።

እርግጥ ነው ንጉሰ ነገስቱ በኢትዮጵያ የአንድነት ጉዞና በህዝቧ ስልጣኔ ጅማሮ ላይ ጋሬጣ የሆነው ሁሉ በፍቅርም ሆነ በጠብ ለማስተካከል ሞክረዋል። እርግጥ ነው ንጉሰ ነገስቱ የኢትዮጵያውያንን ክብርና የሃገራቸውን ልዕልና የሚያዋርድና የሚነካ ማንኛውንም ነገር በኢትዮጵያዊ ቆራጥነት ለመገዳደርና ብሎም ማንኛውንም ዋጋ ከፍሎ ለማስተካከል ወደ ኋላ እንደማይሉ የራሳቸውን ህይወት አሳልፈው በመስጠት አስመስክረዋል። በዘመናቸው ሁሉ ያደረጓቸው ተግባራት አንዳቸውም ከእራሳቸው የግል ክብርና የስልጣን ጥማት ተነስተው እንዳልሆነ ከባላንጣዎቻቸው ልጆች መካከል አፄ ዩሃንስንና አፄ ምኒልክን ከበኩር ልጃቸው ከራስ መሸሻ እኩል አስተምረው ለንግስና ብቁ አድርገው አልፈዋል። በኢትዮጵያና በልጆቿ ህልውና ላይ ግን ቀልድ የለም! ኢትዮጵያዊ ቆራጥነት የግድ ይላልና ነው!

የተከበራችሁ ወገኖቼ!

በሃገራችን ልጆች አማካኝነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህን እውነታ የሚያረጋግጡ አዳዲስ መረጃዎች እየወጡ እንደሆነ እያየሁ ነው። በቅርቡም ለህትመት የሚበቁ አዳዲስ መረጃዎችን የያዙ መፃህፍት በዝግጅት ላይ እንዳሉ በግሌ አውቃለሁና ለሁሉም ጊዜ ይስጠን። ለዛሬ ግን የንጉሰ ነገስቱን ኢትዮጵያዊ ቆራጥነትና ሩህሩህነታቸውን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ አንድ አጭር ገጠመኝ ላንሳና ወደ ሚቀጥለው ርእሴ ልለፍ።

ነገሩ የተፈጠረው ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ወደ ጎጀም በዘመቱ ጊዜ ነበር። ጎጃም ላይ በተደረገው የወንድማማቾች አሳዛኝ ጦርነት ቤተሰቦቿ የሞቱባት አንዲት ስመጥር እመቤት ነበረች። ይህች ሰዎቿን ያጣች እናት የንጉሰ ነገስቱ ጦር በዘመተበት ቦታ ሁሉ እየተከተለች፣ የንጉሰ ነገስቱ ድንኳን በተተከለበት ቦታ ሁሉ እየደረሰች እርሳቸውን ትሳደብና ትራገም ነበር አሉ። ይህ ጉዞዋ እስከ መጨረሻው የመቅደላ ስንብት ድረስ አልተቋረጠም ነበር ይባላል። በዚህ ሁሉ ጉዞዋና ክልትሟ ወቅት ቀለብ የሚሰፈርላትና ድንኳን የሚተከልላት እኩል ከንጉሰ ነገስቱ አገልጋዮች ጋር ነበር። በንጉሰ ነገስቱ ላይ በምታወርዳቸው የስድብና የእርግማን ናዳ ምክንያት እንድም አገልጋይና አሽከር በክፉ ተመልክቷትም ሆነ ችግር አድርሶባት አያውቅም ነበር ይባላል። ይሁን እንጂ ምንም ችግር ሳያጋጥማት የቀረው በዙሪያዋ አቅባጭና እወደድ ባይ የንጉስ ባለሟል ጠፍቶ ሳይሆን ንጉሰ ነገስቱ በቀጥታ ለሰራዊቱ ባስተላለፉት ቀጭን ትዕዛዝና መልዕክት ምክንያት ነበር። ትዕዛዙም ይህቺን ወይዘሮ እኔን በየደረስኩበት እየተከተለች ብትረግመኝና ብትሰድበኝ ፍርዷ ነው። የምትወዳቸውን ቤተሰቦቿን ስላሳጣናት ነው። ስለዚህ እርሷን ማንም ሰው እንዳይነካት፣ የእለት ቀለቧንና፣ የአመት ልብሷን ከእኔ አገልጋዮች እንደ አንዱ እኩል ይደረግላት” ብለው በማወጃቸው ነበር ይባላል። ታዲያ ይህቺ ወይዘሮ በእርሳቸው ኢትዮጵያዊ ቆራጥነትና ደግነት ምክንያት ጥላቻዋ በፍቅር ተቀይሮ እስከ መቅደላ ፍፃሜ አብራቸው የተጓዘች ስትሆነ የንጉሰ ነገስቱን ሹሩባ በእንግሊዞች እንዳይዘረፍ በብርቱ የታገለችና በከፊል ማስቀረት የቻለች መሆኗ ይነገራል።

4. ንጉሰ ነገስቱ ታማኝ መሪና፣ እውነተኛ ጓደኛ ነበሩ !

ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ለእናታቸው ብቸኛ ልጅ ነበሩና በአብዛኛው “አንድ ለእናቱ” እየተባሉ ሲጠሩ እንሰማለን። ሺ ለጠላቱም ሳይረሳ ማለቴ ነው።

ታዲያ በሽፍትነት ዘመናቸው ከተዋወቋቸው ጓደኞቻቸው መካከል ራስ እንግዳ፣ ፊታውራሪ ገብርዬ ጎሹ፣ ደጃዝማች አለሜና፣ ደጃዝማች ገልሞን ከእናትም ልጅ በላይ እጅግ የሚወዷቸው ወንድሞቻቸው እንደነበሩ በስፋት የተፃፈና ተደጋግሞ የምንሰማው ነገር ነው።

ንጉሰ ነገስቱ ከእነዚህ ወንድሞቻቸው ጋር እንደ ቀደመ ጓደኝነታቸው የፈረስ ጉግስ ሳይቀር በነፃነት እንደ ሚጫወቱና እነ ፊታውራሪ ገብርዬም ልክ እንደ ባልንጀር በንጉሰ ነገስቱ የግል ህይወት ድረስ ጣልቃ ገብተው አስተያየትና ሃሳብ እንደሚሰጡ እየሰማሁ አድጌያለሁ።

ከትንሿ የእረፍትና የቤተሰባዊ ጊዜያቸው ተመልሰው ወደ ስራቸው ሲሰማሩ ንጉሰ ነገስት አፄ ቴዎድሮስ የንጉሰ ነገስትነት ቦታቸውን ይዘው ይመራሉ፣ እነ ፊታውራሪ ገብርዬም ቦታ ቦታቸውን ይዘው የመሪያቸውን ትዕዛዝና ውሳኔ ያስፈፅማሉ። ይህ ባህሪያቸው ከሽፍትነት ዘመን እስከ መጨረሻይቱ የመቅደላ ስንብት ድረስ ያልተለያቸው ሲሆን፤ ይህ ደግሞ ከእርሳቸው አብራክ ለተገኘን ልጆቻቸው ብቻ ሳይሆን ማስተዋልን ገንዘብ ላደረገ ትውልድ ሁሉ እንደ እንቁ ሲያበራለት የሚኖር የእውነተኛ ጓደኛና የታማኝ መሪ ባህሪያትንና ስብዕናን የሚያሳይ የህይወት መርህ ሆኖ ይሰማኛል።

የተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ልጆች!

ይህን የተሰጠኝ የመናገር እድል በጣፋጭ ማስታወሻ ልሰርና የዛሬውን መልዕክቴን ልቋጭ።

ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ጓደኞቻቸውን እጅግ የሚያፈቅሩና፣ በታማኝነትና በብቃት ሲመሩ ያለፉ እውነተኛ ወንድምና ታማኝ ንጉሰ ነገስት ሆነው የመጨረሻዋ የመቅደላ ስንብት ላይ ደርሰዋል። መቀደላ ላይ የሆነው ሁሉ ቀደም ሲል የኖሩበትን ህይወት በፅኑ ፈተና ተፈትነው በታላቅ ድል አድራጊነት መወጣት ነው።

በእኔ እይታና እምነት የእንግሊዝ ወረራ አንድ ታላቅና ሉዓላዊት ሃገርን በመድፈርና በመውረር ብቻ የሚመዘን ሳይሆን መተኪያ የሌላቸውንና የኢትዮጵያ ብርቅዬ ጀግኖች የነበሩትን እነ ራስ እንግዳን፣ ገብርዬን፣ እነ አለሜን፣ እነ ገልሞንና፣ ሌሎችን ያለርህራሄ ቀርጥፎ የበላ የጨካኞች ዘመቻ ነው። በዚህች ክፉ ቀን ንጉሰ ነገስቱ እጅግ እንደ ተጨነቁና ፈፅመው እንዳዘኑ መገመት አያዳግትም። ምክንያቱም የእድሜ ልክ የትግል ጓደኞቻቸውንና ወንድሞቻቸውን በወራሪዎች ተነጥቀዋልና ነው። ምን አልባትም ኢትዮጵያዊ የወንድ ወንድ ናቸውና በአደባባይ አያለቅሱ ይሆናል እንጂ ውስጣቸው ደም እንዳነባ መገመት ቀላል ነው። እናም የቀደሙ ወንድሞቻቸውንና አሽከሮቻቸውን ተከትለው መሄድን መረጡ። በህይወት እያሉ ተለያይተው አያውቁምና በሞታቸውም ላይነጣጠሉ ቆረጡ። ይህ የመጨረሻ ውሳኔ የቀረው ደግሞ የንጉሰ ነገስቱ እንጂ ሌሎቹማ ቅድመው ሄደዋል። አይተው በማይጠግቡት በህፃኑ በልዑል አለማየሁ ጨከኑበት፣ በክብርት ሚስታቸው በእቴጌ ጥሩወርቅም ጨከኑባቸው። የመጨረሻ ውሳኔያቸው ላይ የሞታቸውን ለሃገርና ለትውልድ የተረፈ የክብር ማህተም አሳረፉበት። አባታችን ከምንም በላይ፣ ከቤተሰቦቻቸውም በላይ፣ ከእራሳቸውም ህይወት በላይ፣ አብረዋቸው ረጅሙን ሃገራዊ የትግል ጉዞ ለጀምሩ ጓደኞቻቸውና አሽከሮቻቸው እስከ መጨረሻው ህቅታ ድረስ የታመኑ ጓደኛና መሪ ሆነው በክብር አለፈዋል።

የተወደዳችሁ የሃገሬ ልጆች!

ዛሬ ኢትዮጵያ ሃገራችንና መላው ህዝቧ አባቶቻችን በታላቅ ተጋድሎና በክቡር መስዋዕትነታቸው ከአደረሱን የአንድነትና የክብር ማማ ላይ ወርደንና ተዋርደን ወደ ጨለማውና ደካሞች ወደ ነበርንበት የዘመነ መሳፍንት ስርዓት ቁልቁል የወረድንበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብዬ አምናለሁ። ስለሆነም፦

ዛሬም እንደ አለፈው የጀግንነት ዘምናችን በኢትዮጵያዊ ቆራጥነት ተነስተን የሃገራችን ኢትዮትዮጵያን ሉዓላዊነት የማዳን፣ አንድነቷን የማፅናት፣ የህዝቧን ክብር የማስመለስና፣ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ አንድነትና ሰላም የመጠበቅና የማስጠበቅ ታሪካዊ ግዴታና ሃላፊነት ተጥሎብናል ብዬ አምናለሁ።

ትላንት ዘመነ መሳፍንት ኢትዮጵያን የመበታተን አደጋ ላይ ጣላትን እንጂ ከውድቀት እንዳልታደጋት ሁሉ ዛሬም ታላቋን ኢትዮጵያ በቋንቋና በጎሳ ከፋፍሎ ያዳከማትና ሊያጠፋት እጫፍ የደረሰው ህወሃት መራሹ እኩይ ስርዓት ኢትዮጵያንና ኢትዮያዊነትን አደጋ ላይ ጣላት እንጂ ከገባችበት የጥፋት አዘቅት ውስጥ ሊያወጣትም ሆነ ከሞት ሊታደጋት አይቻለውም። ምክንያቱም የህወሃት መራሹ ስርዓት እንደ ዘመነ መሳፍንት ስርዓት ባህሪውም ሆነ ውጤቱ መለያየትና መጠፋፋት በመሆኑ ነው።

ይልቁንስ ውድ ወገኖቼ!

በሽርፍራፊ ድሎች ሳንዘናጋ፣

ዛሬ የተጎናጸፍነውን የህዝብ አቅምና ጉልበት አሰባስበንና አጠናክረን ወደ ድል አድራጊነታችን መዝመት ያሻናል፣

ዛሬ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን አጥፊዎች ድል የነሱበትና ሃገራቸንን ከጥፋትና ከውድቀት የታደጉበት የትግል ስልትና አደረጃጀት ላይ የታነጸ “አገር አድን” ንቅናቄና ሃይል ያስፈልገናል፣

ዛሬ እንደ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ያለ ታላቅ ባለ ራዕይ፣ ቆራጥ ኢትዮጵያዊ፣ ታማኝ፣ ሩህርህና ደግ መሪ ያሻናል፣

ዛሬ እንደ እነ ራስ እንግዳ፣ ፊታውራሪ ገብርዬ፣ ደጃዝማች አለሜ፣ ቀኛዝማች ገልሞ፣ … ወዘተ እንዲህ ያለ ብዙ የብዙ የሆኑ ኢትዮጵያዊ የጦር ገበሬዎችና ታማኝ ጓደኞች ያስፈልጉናል፣

ዛሬ ምድሪቱ አፍ አውጥታ ልጆቼ አድኑኝ እያለች ትጣራለች! ዛሬ ህዝባችን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ከጥፋት አድኑኝ እያለ ነውና በአንድነት እንድረስላቸው፣

ከአገርና ትውልድ ከማዳን ትግላችን ጋር ወደፊት!

እግዚአብሔር የኢትዮጵያንና የህዝቧን አንድነትና ሰላም ያፅና!

አመሰግናለሁ!

ግንቦት 4 2010 ዓ.ም