Home Uncategorized ልሳነ ግፉዓን “ከዚህ ወዴት” በሚለው ጭብጥ ዙሪያ የመወያያ ሃሳብ ስለማቅረብ

ልሳነ ግፉዓን “ከዚህ ወዴት” በሚለው ጭብጥ ዙሪያ የመወያያ ሃሳብ ስለማቅረብ

0

ጉዳዩ፡ “ልሳነ ግፉዓን ከዚህ ወዴት?”

መቅድም

በቅድሚያ እራሱን “የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ድርጅት” እያለ የሚጠራው ወራሪና ተስፋፊ ቡድን የተከዜን ወንዝ ተሻግሮ የጎንደርን ታሪካዊ መሬቶች በሃይል ለመያዝ ከሞከረበት ጊዜ ጀምሮ በሚቻላችሁ ሁሉ በመቃወም ውድ ህይወታችሁን ለሰዋችሁ፣ ወርቃማውን የወጣትነትና የጎልማሳነት ዘመናችሁን በእስር፣ በስቃይና፣ በስደት ለማሳለፍ የተገደዳችሁ፣ ትዳራችሁንና ህፃናት ልጆቻችሁን ያለ አባትና አሳዳጊ ለመተው የተፈረደባችሁ፣ አዛውንትና ደካማ ወላጆቻችሁን ያለጧሪ ለቀሩባችሁ፣ ይልቁንም የፈራችሁት መከራና ጥፍት በወልቃይት፣ በጠገዴና፣ በጠለምት ማህበረስብ ላይ ደርሶ፤ የቀደሙት አባቶቻችሁ እርስት የትግሬ ሰፋሪ መፈንጫና መገልሞቻ ሆኖ ባያችሁ ጊዜ ሞትን መርጣችሁ በዱር በገደሉ ለምትዋደቁ፣ በየማሰቃያው ስፍራ መራር ግፍና መከራ ለምትቀበሉ፣ በያላችሁበት ሆናችሁ ጠላትን ለማንበርከክ የአቅማችሁን ለምታደርጉ ሁሉ ምንም እንኳ ትግሉ መራር ቢሆንም መስዋዕትነታችሁና ድካማችሁ ፍሬ አፍርቶ የወልቃይት ጥያቄ የተነሳችሁለትን ግብ ሳይመታ ላይቀለበስ ትውልድ ላይ ታትሟልና በሰማይም ሆነ በምድር ደስ ይበላችሁ።      

በማስቀጠልም ከቀደሙት ጀግኖቻችን የተረከባችሁትን የህልውና ትግል ለጠላት ባደሩ ተንበርካኪዎችና ተላላኪዎች ሳይበረዝና ሳይከለስ  ጠብቃችሁ፣ ተቋማዊ ቅርፅ በማስያዝ ድርጅት መስርታችሁ፣ በብዙ እንግልትና መሰናክል ውስጥ አልፋችሁ፣ ከልሳነ ግፉዓን ጋር በይፋ መስራት እስከ ጀመርኩብት ጊዜ ድረስ የድርጅቱን ህልውና፣ ጥራትና፣ ብቃት በአስተማማኝ ሁኔታ ጠብቃችሁ ላቆያችሁኝ የልሳነ ግፉዓን አመራሮችና መስራች አባላት የአክብሮት ምስጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ።

እኔ ወደ ሰሜን አሜሪካን በስደት ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ያመንኩትና በይፋ አብሬው የሰራሁት ድርጀት ቢኖር ልሳነ ግፉዓን ብቻ ነው። ምክንያቱም ልሳነ ግፉዓን የቆመለት አላማና የሚከተለው የትግል ስልት/strategy/፣ የመሪዎቹና የአባላቱ ታማኝነትና፣ ጨዋነት፣ ፋሽስቱንና ተስፋፊውን የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ድርጅት አምርሮ ለመታገል ያላቸው ብቃትና ቁርጠኝነት፣ ይልቁንም ለህወሃት የስለላ መዋቅርና ለተመሳሳይ ሰርጎ ገቦች በፍፁም የማይከፈትና ለዘለዓለሙ የተዘጋ የምስጢር አጠባብቅ ዘዴ ባለቤት መሆናቸው ሁሌም ያረካኛል።

በአለፉት 7 አመታት (2010 መጨረሻ ጀምሮ) ከልሳነ ግፉዓን ጋር ያደረኩትን የትግል ጉዞና በሂደቱም ያሳለፍኳቸውን ውጣ ውረዶች፣ እንቅልፋ አልባ ሌሊቶችና እረፍት አልባ ቀናት፣ በብዙ ጭንቀትና ሰቀቀን ያገኘናቸውን መረጃዎች፣ በአሜኬላ በተሞላው የህወሃት መንደር ለተልዕኮ የተሰማሩ ወገኖች ያስመዘገቧቸው ድሎች፣ በዚህ ሁሉ ሂደት ያጣጣምናቸውን መራር ሽንፈቶችና ጣፋጭ ድሎች … ወዘተ ሳስብ ልቤ በሃሴትና በቁጭት እኩል ትነድብኛለች። ይህን ስሜት ለእኔ ፍፁም ልዩ ነው! ለዚህም ነው ለልሳነ ግፉዓንና አብሪያቸው ለታገልኩት ጓዶቼ ሁሉ ልዩና እስከመጨረሻው የታመነ ፍቅርና አክብሮት እንዲኖረኝ ያስገደደኝ።

ወደ ልሳነ ግፉዓን ስቀላቀል በእድሜም ሆነ በትግል ልምድ ጎረምሳ ነበርኩ። ዛሬ ከ 7 አምታት በኋላ እራሴን ስገመግምና የመጣሁበትን የህይወት ጎዳና ወደኋላ ስቃኝ ከትላንቱ በብዙ የተለወጥኩ ይመስለኛል። ብዙ ተምሪያለሁ፣ ብዙም አውቂያለሁ። በእግዚአብሄር መልካም ፈቃድ ወደፊት ገና ብዙ እማራለሁ! ብዙ አውቃለሁ! ብዙም እሰራለሁ! ምስጋና በራቸውን ከፍተው በፍቅርና በአክብሮት ተቀብለው ወገኔን ከጥፋት ለመታደግ በሚደረገው የምር ትግል ውስጥ የአቅሜን እንዳበረክትና የድርሻዬን እንድወጣ እድሉን ለሰጡኝ ሁሉ ይሁን።

ዛሬ ላይ ሆነን ወደ ራሳችን ስንመለከት

እኔም ወደ ልሳነ ግፉዓን ከተቀላቀልኩና ትግሉም እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ብዙዎችን ከጎናችን ማሰለፍ እንደቻልን አውቃለሁ። ብዙዎችም ልሳነ ግፉዓን ባነገባቸው አጀንዳዎች ዙሪያ ተሰልፈው እየተጋደሉ እንደሚገኙ አውቃለሁ። ነገ እልፎች ከጎናችን እንደሚሰልፉ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ይልቁንም በዚህ ሰአት ሌት ከቀን ጎትጉተንና የእኛን ድርጅታዊ አመራር አምኖ ወደ ትግሉ ሜዳ ያስገባነው ወገናችን ከፊትና ከኋላ በመሆን እንደ ከያኒው “… ወደ ኋላ የለም! ወደ ኋላ!” እያለ በፅናትና በቁርጠኝነት ወደ ታላቁ ድል እንድንገሰግስ እየገፋን ያለ ይመስለኛል።

በእኔ እምነት ዛሬ በአለፉት የትግል አመታት የመጣንበትን መንገድ ቆም ብለን የምንገመግምበትና ቀጣዩንም የትግል አቅጣጫ የምንተልምበት ምቹና ትክክለኛ ወቅት ነው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ነገ ወደ ድርጅታችን የሚመጣውን የታጋይ ህዝብ ብዛት መሸከም የሚችል ድርጅታዊ መዋቅር መዘርጋትና ከዚሁም ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የህዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ማስተናገድና በብቃት መምራት የሚችል ብቁ አመራር መፍጠር የዛሬና በሚቀጥሉት ጥቂት ጊዜያት ውስጥ ከስር ከስር የሚሰራ ተቀዳሚ ስራ እንጂ ነገ በህዝብ ጥያቄ፣ በአባላት ብዛትና፣ በስራ መደራረብ ምክንያት እራሱን በእራሱ አፍኖ የሚገድል ባለተራው ኢትዮጵያዊ ድርጅት እስክንሆን ድረስ መጠበቅ ያለብን አይመስለኝም። እዚህ ላይ “ሰርገኛ መጣ፣ በርበሬ ቀንጥሱ” የምትለውን የማንቂያ ደወል መጠቀም አይከፍም ።

ዛሬ ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን አንግቦ የተነሳቸውንና የወልቃይት የጠገዴና የጠለምት ህዝብ ሰቆቃና የድረሱለኝ ጥሪ ልሳን መሆን፣ በግፍ ለተነጠቃቸው ሰብአዊ መብቶቹ መከበር ግንባር ቀደም ተሟጋች የመሆን፣ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ አጀንዳዎችና አላማዎቹን በሚያኮራና ታሪካዊ በሆነ ደረጃ አተሳክቷል ብዬ አምናለሁ። በዚህ አጋጣሚ ለመላው አባላቱ እና አመራሮቹ እንኳን ደስ ያላችሁ ማለትን እወዳለሁ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ህዝባዊ ትግሉ ከየአቅጣጫው የቀሰቀሰውና በዙሪያው ያሰለፈው የህዝብ ብዛትና እነዚህ ትግሉን የተቀላቀሉ ወገኖቻችን  ይዘዋቸው የተነሷቸው የግልና የጋራ ብሶቶቻቸውና ጥያቄዎቻቸው ፍትሃዊ ምላሽ እንዲያገኙ አብሮ የመታገልና የማታገል የሞራልም ሆነ የዜግነት ወገናዊና ታሪካዊ ግዴታ አለብን ብዬ አምናለሁ። ስለሆነም ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን ከላይ ያነሳኋቸውንና በመጣጥፌ ውስጥ በዝርዝር የምመለስባቸውን ግዴታዎች ከቆመለት አላማና ራዕይ ጋር በማገናዘብ ዘመኑን የዋጀ ድርጅታዊ የማሻሻያ እርምጃዎች ሊወስድ የሚገባ ይመስለኛል። ዛሬ አሁን በደረስንበት የእድገት እና የአሸናፊነት ልዕልና ላይ ሆነን ስንነጋገር በዋናነት መነሳት ይኖርባቸዋል ከምላቸው አበይት ቁምነገሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ

  1. ልሳነ ግፉዓን ዋና ዋና አላማዎቹ ምን ምን ነበሩ? የትኞቹን አሳክቷል?
  2. የድርጅታችን የስኬት ምስጢሮቹ ምን ምን ናቸው?
  3. ድርጅታችን ከተመሰረተበት ከ2009 ጀምሮ በጉዞው የገጠሙት ፈተናዎች ምን ምን ነበሩ? እንዴትስ አለፋቸው?
  4. የልሳነ ግፉዓን ወደ ፊት የሚጠብቁት ተግዳሮቶች ምን ምን ናቸው?
  5. ልሳነ ግፉዓን ከዚህ ወዴት? ቀጣዩ የትግል ጉዞና አካሄድ ምን መሆን ይኖርበታል? የሚሉት ናቸው።

የልሳነ ግፉዓን ከቆመላቸው አላማዎችና ግቦች አንፃር ለህዝባችን ምን አይነት ስኬቶችና ድሎች አበርክቷል?

1ኛ. ልሳነ ግፉዓን ዋና ዋና አላማዎቹ ምን ምን ነበሩ? የትኞቹን አሳክቷል?

በዋናነት ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን በግንባር ቀደምትነት አንግቧቸው ከተሳው አበይት አላማዎች በላቀ ሁኔታ የጠላትን ትክክለኛ አላማ፣ ባህሪና፣ አካሄድ በቅጡ ከመረዳትና ጠላትን ድል ለመንሳት የሚያስችል ተመጣጣኝ የትግል ስልትና ዘዴ ቀርፆ መንቀሳቀስ ለስኬታማነታችን እጅግ አስፈላጊና ወሳኝ እንደ ነበር አፅንኦት ሰጥቶ የሰራበት ጉዳይ ነበር። ስለሆነም የሚከተሉትን ግዙፍ ተግባራት ለመከወንና አላማዎቹንም በሚያስደስት ሁኔታ ለማሳካት ችሏል።

ሀ. የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ በህወሃት የተከፈተበትን ወረራና ከፊቱ የተደቀነበትን የዘር ማፅዳት ጥፋት በትክክል እንዲረዳና  እራሱንና መጭውን ትውልድ ከጥፋት ለመታደግ በቁርጠኝነት ለትግል እንዲነሳ ማስቻል፤

የወልቃይት ህዝብ በትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ድርጅት በኩል የታወጀበትን ታሪክ ነጋሪ አዛውንቱን በማጥፋት፣ ጎልማሳውን በማሰር፣ በመሰወር፣ በማሳደድ፣ በመግደል ዕርስትና ትውልድ ጠባቂ በማሳጣት፣ ታሪክ ተረካቢ የሆነውን ወጣቱን ትውልድ ህወሃት በፈበረካቸው ሃሰተኛና ልብወልድ ትግሪያዊ ተረታ-ተረቶች በመበረዝ፣ ከደም-መላሽ ወንድሙና አለኝታው ከሆነው የጎንደር ህዝብ በመነጠል፣ አማራዊ ማንነቱንና ኢትዮጵያዊ ኩራቱን በማጠልሸትና በማጥፋት፣ ለም መሬቱን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ ከትግራይ በመጡ የትግሬ ሰፋሪዎች በማስወረር፣ በአጠቃላይ ዘሩን የማፅዳትና በትግሪያዊነት የመተካቱን ሴራና ሂደት በቅጡ ተረድቶ ወቅቱ የሚጠይቀውን ግንዛቤ እንዲኖረውና በጉዳዩ ላይ ግልፅ አቋም እንዲይዝ በማስቻል ለትግል እንዲነሳ ማድረግ እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ ነበር። ምክንያቱም፦

  1. ችግሩን አስመልክቶ በልሳነ ግፉዓን በኩል ይቀርብ የነበረው ትክክለኛ ትንታኔ እና መረዳት ከህዝባችንም ሆነ በጉዳዩ ላይ እውቀትና ልምድ ካላቸው ምሁራንና ፖለቲከኞች በእጅጉ የላቀ በመሆኑ የልሳነ ግፉዓን አቀራረብ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር በእጅጉ የማይመጣጠን እና በጣም የራቀ ነው የሚል የተዛባ ግንዛቤና አቋም በብዙዎች ዘንድ በመያዙ፤
  2. የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችና ሃገር ቤት ውስጥ በሚያካሂዷቸው የእርሻና የንግድ እንቅስቃሴዎች ምክንያት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለህወሃት የተንበረከኩ ኣንዳንድ ግለሰቦች በማህበረሰቡ ውስጥ የፈጠሩት የጥቅመኝነት ባህልና የመከፋፈል ሴራ፤
  3. ከወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ ከአቶ ፀጋዬ አስማማውና፣ ከአቶ ፈረደ የሽወንድም ከመሳሰሉ የህወሃት ተላልኪዎችና አገልጋዮች ጋር የጠበቀ ግንኙነት በነበራቸው ግለሰቦች አማካኝነት ወደ ህዝባችን የሚሰራጨው የመከፋፈልና የማበጣበጥ ሴራ ቤተሰባዊ ባህሪ የተላበሰ በመሆኑ ተፅዕኖው ከባድና ውስብስብ ስለነበር፤
  4. ቁጥራቸው አነስተኛም ቢሆንም እንኳ ከትግሬ ዘር የተወለዱና ከትግሬ ጋር የተጋቡ የወልቃይት ተወላጆች በማህበረሰባችን ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው የግለሰቦችን ትግሪያዊ ማንነት ከህዝብ ማንነት ጋር በመቀላቀልና በማምታታት የህወሃትን የመስፋፋትና አማራን የማጥፋት ሴራ ለማክሸፍ የሚደረገውን ትግል ህዝባችን በሙሉ ሃይሉና ልቡ እንዳይታገል እንቅፋት በመሆን ሊያደነቃቅፉት ይውተረተሩ ስለነበር ነው።

ስለሆነም ህዝባችን በጠራ የትግል አቋምና የፀና አንድነት ውስጥ በመሆን ሊያጠፋው የመጣውን ጠላት በሙሉ ሃይሉ አምርሮ እንዳይታገል ማነቆ የሆኑትን ሳንካዎች በማጋለጥ ከትግሉ ሜዳ ጠራርጎ ማስወገድና ህዝባችን “እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ አንደበት ተናጋሪ” በመሆን በቁርጥኝነት ወደ ትግሉ ሜዳ እንዲገባ ማስቻል የድርጅታችን ዋነኛ ተቀዳሚ አጀንዳ ነበር።

በመሆኑም ድርጅታችን በህዝባችን ውስጥ ባደረገው የውስጥ ለውስጥ መራራ ትግልና ያላሰለሰ ጥረት እንክርዳዶቹን ከንፁሁና ከታጋዩ ህዝብ መካከል ለይቶ በማውጣት ጠላት ወደ ድርጅታችን ሰርጎ ሊገባበት የሚችለውን ቀዳዳ ሁሉ በመድፈን በማይቀረው ፍትሃዊ ትግል ውስጥ የበኩላቸውንና አቅማቸው የሚፈቅደውን አስተዋፅዕ ለማበርከት ወደ ድርጅታችን የተቀላቀለውን ታጋይ ህዝብ ደህንነቱና ምስጢሩ በአስተማማኝነት በተጠበቀ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንዲታገል ማስቻል ሙሉ ለሙሉ ተችሏል። ለዚህም የድርጅታችን አመራሮችና አባላት ላቅ ያለ ምስጋና ይጋባቸዋል።

ለ. ለወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ እውነተኛ ድምፅ መሆን

ተስፋፊውና ፋሽስቱ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ድርጅት የጎንደርን ለምና ታሪካዊ መሬቶች ወደ ትግራይ በማካለል አካባቢውን ትግሪያዊ ለማድረግ በያዘው እኩይ አላማ ምክንያት የወልቃይት የጠገዴና የጠለምትን ህዝብን ከአካባቢው በማፅዳት ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ቁጥር ያለው የትግራይ ሰፋሪ በአካባቢው በማስፈር ነባሩን የአማራ ህዝብና ዘር እንዲጠፋና በትግሪያዊነት እንዲተካ በማድረግ በህባችን ላይ ከፍተኛ ግፍና በደል ሲፈፅን ኖሯል።

ምንም እንኳ ህዝባችን ይህን እኩይ የዘር ማፅዳት ወንጀል ለመቀልበስ የሚችለውን ሁሉ ቢያደርግም “ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል” እንዲሉ ጊዜ የሰጠው ፍሽስቱ ህወሃት ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ወገኖቻችን የሰቆቃ ድምፃቸው ለኢትዮጵያም ህዝብ ሆነ ለዓለም ማህበረሰብ እንዳይሰማ በማድረግ ለጀምላ እስር፣ ለመራር ስቃይ፣ ለግፋዊ ግድያና፣ ለመጠነ ሰፊ ስደት ዳርጓቸዋል።

ህወሃት የሃገሪቱን መንግስታዊ ስልጣንና ሃብት ከተቆጣጠረ ጀምሮ “ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት” የሚለው ስምና በእነዚህ አካባቢዎች የምንኖር የጎንደር ተወላጆችን አማራዊ ዘር ጨርሶ ከምድረ-ገፅ የማጥፋቱን ስራ በረቀቀና በተጠና ሁኔታ ማከናወኑ ያሳሰባቸው በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ወንድሞቻችን የወሰዱት ታሪካዊ እርምጃ ቢኖር “ልሳነ ግፉዓን” የሚል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ማቋቋም ነበር። በመቀጠልም ተቀዳሚ ተግባራቸው ያደረጉት በዚህ ድርጅት ዙሪያ በመሰባሰብ ህዝባችን ጨርሶ ከመጥፋቱ በፊት የህዝባችንን የሰቆቃ ድምፅ ለኢትዮጵያና ለዓለም ሰላምና ፍትህ ወዳድ ህዝቦች፣ የፍትህና የሰብአዊ መብት አስከባሪ አካላትና፣ እውነተኛ ጋዜጠኞች ዘንድ በማድረስ የህወሃት የዘር ማፅዳት ሴራና ወንጀል በተጨባጭ መረጃ ማጋለጥ ነበር።

በዚህም መሰረት የልሳነ ግፉዓን አመራሮችና አባላት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና የውይይት መድረኮች በመቅረብ የወልቃይትን ህዝብ የድረሱልኝ ጥሪ ላልሰማው ወገናችን ሁሉ በማሰማት፤ በተለይም በኢሳት ቴሌቪዥንና ሬድዮ፣ በግንቦት 7 ሬዲዮ፣ በጀርመን ድምፅ ሬዲዮ፣ በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ፣ እንዲሁም በተለያዩ የአውሮፓና የአሜሪካ ከተሞች በሚገኙ ሬዲዮና የቴሌቪዥ ስርጭቶች ቀርቦ በማስረዳትና ከህዝብ ለሚቀርቡ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት የህዝባችን ጩሃት በሁሉም ዘንድ ያለ አንዳች ገደብ እንዲደመጥ አስችሏል።

በተመሳሳይ መልኩ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ድረ-ገፆችና ብሎጎችን በመጠቀም የወልቃይት ጩሃት እውነተኛ የንፁሃን የሰቆቃ ድምፅ መሆኑንና ጉዳዩ ከወሬ በዘለለ ሁኔታ በተጨባጭ ሰነዶችና በትክክለኛ መረጃዎች የተደገፈ እንደሆነ የሚያስገነዝቡና የሚያሳስቡ የተለያዩና ተከታታይነት ያላቸውን ፅሁፎችና መግለጫዎችን በማቅረብ ግንዛቤ እንዲፈጠር ያደረገ ሲሆን፣ በህወሃትና በተላላኪዎቹ በኩል የሚቀርቡትን ሃሰተኛ መግለጫዎችና ሰነዶችን ታሪካዊነታቸው በተረጋገጠላቸው እውነተኛ ማስረጃዎች ማጋለጥና በዚህም የህዝባችን የደረሱልኝ ጩሃትና የሚያካሂደው ፍትሃዊ ትግል በሁሉም ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረግ ተችሏል።

ከሁሉም በላይ የወልቃይት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘትና የልሳነ ግፉዓን እውነተኛ የህዝብ ድምፅ መሆን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጠርው ግንዛቤና ይህንንም ተከትሎ ከየአቅጣጫው የቀሰቀሰው ህዝባዊ ጥያቄና ጫና ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ፋሽስቱና ተስፋፊው የህወሃት ወራሪ ቡድን  በሃይል ወደ ትግራይ የከለላቸውን የወልቃይት የጠገዴና የጠለምት ለምና ታሪካዊ የጎንደር መሬቶች ላይ በተዛባና በሃሰተኛ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ ቅስቅሳ ላይ እንዲጠመድና በታሪክ “ወልቃይት የትግራይ አካል ነበረች” ወደሚል የአደባባይ ቅስቀሳና ሙግት ውስጥ ተገዶ እንዲገባ ማድረግ ተችሏል። በዚህም  ምክንያት ህዝባችን ከሁሉም በላይ የሆነውን ድል እንዲጎናፀፍ አስችሎታል።  ይሃውም፦

  1. ኢትዮጵያዊ ምሁራን፣ የሃገር ሽማግሌዎችና፣ ታሪክ አዋቂዎች በህዝባችን ትግል ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊና ባለቤት የመሆን እድልን ፈጥሮላቸዋል። ስለሆነም የህወሃትን የሃሰት ቅስቀሳና አስተምህሮት በእውነተኛና በታሪክ በተደገፉ ማስረጃዎችና ትክክለኛ አስተምህሮት በአደባባይ እንዲጋለጥና የህወሃት አይን ያወጣ ወረራና ዝርፊያ ህገወጥ መሆኑ በሁሉም ዘንድ እንዲታዎቅ አስችሏል።
  2. ወጣት ምሁራንና ፖለቲከኞች በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ ጥያቄ ላይ ግንዛቤ እንዲያገኙና ትክክለኛ እወቀት ኖሯቸው ከህዝባችን ትግል ጎን እንዲሰለፉ አስችሏል።
  3. እነ ክቡር ልዑል እራስ መንገሻ ስዩምንና አቶ ገብረመድህን አርአያን የመሳሰሉ ታዋቂ የትግራይ ተወላጆችና ፖለቲከኞች በአደባባይ የወልቃይትን ህዝብ ትግል እንዲደግፉና በህወሃት በኩል የሚቀርበውን የሃሰት አስተምህሮ በአደባባይ በፅናት እንዲቃወሙና እውነታውን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያጋልጡ አስችሏቸዋል። በዚህ አጋጣሚ ጋዜጠኛ ተክሌ የኋላን ለመጀመሪያ ጊዜ ለዑል ራስ መንገሻ በጀርመን ድምፅ ላይ በማቅረብ እውነታውን እንዲናገሩ በማድረጉ በግሌ ላመስገነው እወዳለሁ።
  4. ጋዜጠኞችና የታሪክ ምሁራን በወልቃይት ዙሪያ አበክረው ትምህርት እንዲሰጡና የተለያዩ ፕሮግራሞችን እንዲያዘጋጁ መነቃቃትን ፈጥሯል።
  5. ታላላቅ ሚዲያዎች፣ በብዛት ተነባቢ የሆኑ ድረ-ገፆችና፣ ታዋቂ ብሎጎች ላለፉት 5 አመታት ቢያንስ በሳምንት አንዴ በወልቃይት ጉዳይ ዙሪያ የሚዘግቡ ሲሆን፤ ከአለፉት 2 አመታት ወዲህ ግንባር ቀደም ሃገራዊ አጀንዳ ለመሆን ችሏል።

በአጠቃላይ ምንም እንኳ ህወሃት የወልቃይትን ጉዳይ ከኢትዮጵያ ህዝብና ከዓለም ማህበረሰብ እይታ ሰውሮ በፀጥታ ማጥፋትን አቅዶ ለአለፉት 35 ዓመታት ቢሰራም የልሳነ ግፉዓን መነሳት ይህን እኩይ ሴራ ወደ አደባባይ እንዲወጣና ህወሃት ፍፁም በሚሸነፍበት የትግል ሜዳ ውስጥ ተገዶ እንዲገባ አስችሏል። ለዚህም ታላቅ ጥበብና ተጋድሎ የድርጅታችን አመራሮችና አባላት ይልቁንም ከላይ የዘረዘርኳቸው ባለድርሻ አካላት ሊመሰገኑ ይገባል። (ከ2010 ጀምሮ ለህዝብ የቀረቡ ልሳኖች መካከል ለናሙና የመረጥኳቸው እባሪ ላይ ተያይዘዋል)

መ. መረጃዎችን ማሰባሰብና ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ

ፀረ-ህዝብና ፀረ-ሰላም የሆነው የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ቡድን ከታሪካዊ ጠላቶቻችን የተቀበለውን ኢትዮጵያንና ህዝቧን የማዳከምና ብሎም የማጥፋት እኩይ አጀንዳ በተግባር ላይ ማዋል የጀመረው የወልቃይትን ህዝብ በማጥፋት መሬቱ በትግሬ ሰፋሪዎች በማጥለቅለቅ፣ በተቀነባበረ ዘዴ የወልቃይት ሴቶች ለትግሬ ወንዶች እንዲወልዱ በማድረግ፣ የወልቃይትን ታሪካዊ የመንገድና የአካባቢ ስሞች በትግሪያዊ ስም እንዲለወጡ በማድረግ፣ በአጠቃላይ በአካባቢው ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወልቃይት የትግሪዎች ብቸኛ መኖሪያ፣ መበልፀጊያና፣ መፈንጫ እንድትሆን በማድረግ ነበር።

ይህን ዘርፈ ብዙ፣ በፍፁም ጥንቃቄና፣ በዝግ የሚደረግ የዘር ማፅዳት ወንጀል በንቃት ተከታትሎ በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፎ ለህዝብ ማጋለጥና ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ አላማው አድርጎ የተንሳው ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን በዚህ ረገድ የሄደበት መንገድ እጅግ የሚያስመሰግንና የሚያበረታታ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

በተለይም ዛሬ ዛሬ በተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች በኩል በሚወጡ ሰነዶች ላይ በህወሃት የግፍ አገዛዝ ተደብድበው አካላቸው የጎደሉ፣በጨለማ ውስጥ የታሰሩ፣ በድብቅና በአደባባይ የተገደሉና፣ ታፍነው ተወስደው የገቡበት ያለታወቁ ህልቆ መሳፍርት የወልቃይት የጠገዴና የጠለምት ተወላጆች ስም ዝርዝሮች ሁሉም ማለት ይቻላል በልሳነ ግፉዓን በኩል የተሰበሰቡና በተለያዩ ጊዜያት ለህዝብ ይፋ በተደረጉ የድርጅታችን መግለጭዎች አማካኝነት የትሰራጩ መሆናቸውን ስናይ ድርጀታችን ልሳነ ግፉዓን ህወሃት በህዝባችን ላይ ያደረሰውን የዘር ማፅዳት ወንጀል ለማጋለጥና ለወገናችን ሰብአዊ መብቶች መከበር እያደረገ ያለውን ታላቅ ተጋድሎና የወሰደውን የመሪነት ሚና በተጨባጭ የሚያሳይ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

ሰ. የወልቃይትን ጉዳይ በሃገራችን ግንባር ቀደም የመታገያ አጀንዳ እንዲሆን ማስቻል

እነሆ ዛሬ የህዝባችን ትግል ፍሬ አፍርቶ ትላንት ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የት እንዳሉ ጨርሶ የማያውቀውና በተለይም “ወልቃይት” የሚለውን ስም አስተካክሎ እንኳ መጥራት የማይችለው የሃገራችን ህዝብና ፖለቲከኛ ዛሬ ከጎንደር ተራሮች እስከ ሶማሌ በረሃ፣ ከአፋር እስከ ጋምቤላ በሁሉም አቅጣጫ ያለው ወገናችን “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ!” በማለት የሚታገልለትና የሚሞትለት አገር አቀፍ አብይ አጀንዳ ለመሆነ በቅቷል።

ዛሬ የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ በስደት ከኢትዮጵያ ውጭ ለሚገኘው ህዝባችን ከሰሜን አሜሪካ አውራ ጎዳናዎች እስከ አውሮፓ የባቡር ጣቢያዎች በግግር በረዶ ማሃል ሌት ከቀን የሚሰለፍለት፣ ከኒውዚላንድ/አውስትራሊያ ደሴት እስከ እስራኤል የጦር ካምፕ፣ ከሰሜን ሱዳን እስከ ደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ወገኖቻችን ተቀዳሚ ጉዳያቸው ለመሆነ የቻለ ሲሆን፤ ይልቁንም ስለ ወልቃይት ሲባል በቁጣና በምሬት ህወሃት ላይ መነሳት የህዝባችን የአንድነትና የወገንተኝነት መለኪያና መገለጫ፣ የኢትዮጵያዊ ጀግንነት አብይ ምግባር ከሆነ ውሎ አድሯል።

የወልቃይት ህዝብ ጩሃትና ሰቆቃ ዛሬ የአለማችን ሃያላን መንግስታትና ድርጅቶቻቸው ሳይቀሩ ጆሯቸውን የሰጡትና በራቸውን የከፈቱለት ታላቅ የህዝብ ጥያቄ ሆኗል። ከአሜሪካው ሴኔት አስከ እስራኤሉ ከንሴት/Knesset/፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአውሮፓው ፓርላማ፣ የአፍሪካው አንድነት ድርጅት፣ እንዲሁም ሁሉም አለም አቀፍና ሃገር በቀል የሰብአዊ ተሟጋች ድርጅቶች በአንድነት ጥብቅና የቆሙለትና በንቃት የሚከታተሉት ቁልፍ አጀንዳ ነው።

ይልቁንም ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን ካሳካቸው አበይት ተግባራት አንዱና ዋነኛው ሰሚ ላልነበረው ለወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ የሰቆቃ ድምፅ እውነተኛ ድምፅ በመሆን የሰው ዘር በሙሉ እንዲሰማውና አጋር እንዲያገኝ ማድረግ ቢሆንም የሚበልጠው ስኬት ግን ዛሬ በዚህ ትግል ዙሪያ በንቃት የሚሳተፉና የህዝባችንን ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገው ለሚነሱ ህዝባዊ ቁጣዎችና ንቅናቄዎች ሁሉ እርሾ ሆኖ ማገልገል የቻለ ግልፅ፣ ቀጥተኛና፣ መዳረሻው የታወቀ አጀንዳ ቀርፆ ትግሉን በፅኑ መሰረትና ባቡሩንም በትክክለኛ ሃዲዱ ላይ እንዲሸከረከር በማስቻሉ ጭምር ነው።

2ኛ. የድርጅታችን የስኬት ምስጢሮች

ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን ተመጣጣኝ በሆነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ስኬታማ እንዲሆን ካስቻሉት ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ይበልጥ ትርጉምና ተፅዕኖ ፈጥረዋል የምላቸውን ለመጥቀስ እሞክራለሁ።

  1. የጠላትን ሴራና አካሄድ ጠንቅቆ በመረዳት ላይ የተመሰረተ ትክክለኛ የትግል ስትራቴጂ ማውጣትና ያወጣውንም የትግል ስልትና አካሄድ በትክክል ወደ ተግባር መተርጎም በመቻሉ፤
  2. አመራሩ ከአባላቱ ጋር ለቆሙለት አላማ እንደ አንድ ቤተሰብ በፅናትና በቁርጠኝነት በመቆም ትግሉን መምራት በመቻላቸው፤
  3. አባላቱ እና አመራሩ ቀጥተኛ የችግሩ ሰለባዎች በመሆናቸው ከማንኛውም ውጫዊና ውስጣዊ ሴራና ተፅዕኖ የፀዳ አመራር መፍጠር በመቻሉ፤
  4. በአመራሩ በኩል ቅድሚያ የተሰጣቸው ምስጢርን የመጠበቅና ለትግሉ ቅድሚያ ሰጥቶ የመስራት ባህርያት ሙሉ ለሙሉ ተግባር ላይ መዋላቸው፤
  5. የትግራይ ነፃ አውጭ ድርጅትና ተላላኪዎቹን በትክክል የተረዳና የእነሱንም የማያባራ የስለላ ሴራና ፈርጀ ብዙ ጥቃት ለመመከት በድርጅቱ ውስጥ ሙሉ ቁረጠኝነት መኖሩና በቂ ትግል በመደረጉ ናቸው ብዬ አምናለሁ።

3ኛ. ድርጅታችን ከተመሰረተበት ጀምሮ በጉዞው የገጠሙት ፈተናዎች ምን ምን ነበሩ? እንዴትስ አለፋቸው?

ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን እንደ ማንኛውም ድርጅት በጉዞው መካከል መሰናክሎችና ፈተናዎች ሳይገጥሙት አላለፈም። በተለይም የህዝባችንና የሃገራችን ግንባር ቀደም ጠላት ከሆነው የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ቡድን በኩል የሚሰነዘረው ተደጋጋሚ ጥቃትና ፈተና እጀግ ከባድ ነበር። ከነዚህም መካከል ዋና ዋና ያለኳቸውን አራቱን ብቻ በአጭሩ ለማንሳት እሞክራለሁ።

  1. በተለይም ህወሃት በወ/ሮ አዜብ መስፍን ዙሪያ በማሸመቅ ከወልቃይት ህዝብ ጋር ያላትን የስጋ ዝምድና ተጠቅሞ ቀላል የማይባሉ ተላላኪዎችን ማሰማራት ችሎ ነበር። በእነዚህ የህወሃት ፍርፋሪ ለቃሚዎች አማካኝነት የህዝባችንን ህብረትና የመታገል ቁርጠኝነትን የተለያዩ የማማለያ ዘዴዎችና ስጦታዎች በማቅርብ ሲቦረቡር ኖሯል። ይህ ሴራ ወደ ልሳነ ግፉዓን የሚመጡትንና በውስጥም ያሉትን በከፍተኛ ሁኔታ ለማጥመድ ለረዥም ጊዜ የተሰራበት በመሆኑ ይህንንም ሴራ ለማክሸፍ በጥንቃቄና በቀስታ መስራት የግድ ነበር። ይልቁንም በሃገር ቤት ያለውን ወገናችን ደህንነት ከመጠበቅ አንፃር ቅድሚያ በመስጠት ቀድሞ የተዘጋጁትን እቅዶችና ግንኙነቶች ሙሉ በሙሉ መቀየር አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ በጉዟችን ላይ እንቅፋት መፍጠሩ አለቀረም ነበር።

 

  1. በሁለተኝነት ሊጠቀስ የሚችለው ተግዳሮት የአመራሩ የአቅም ውስኑነት ከትግሉ ስፋትና ጥልቀት በዚህም ምክንያት ከሚጠይቀው የሰው ሃይል ብዛትና ጥራት ጋር በፍፁም የሚመጣጠን አልነበረም። በአመራርነት የተቀመጠው ቡድን በቁጥር እጀግ አነስተኛ ሲሆን የሚሰራው ስራ ግን እጅግ የበዛ ነበር። ለምሳሌ ያህል ለመጥቀስ በአንድ በኩል የወልቃይትን ማህበረሰብ በህልውናው ላይ የተጋረጠውን አደጋ በወቅቱ ተረድቶ አቋምና እርምጃ እንዲዎስድ ማስቻል በአንድ በኩል ሲሰራ፤ በተመሳሳይ ወቅት በወልቃይት “የዘር ማፅዳት” ወንጀል እየተፈፀመ ነውና ድረሱልን ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ መጮህና ሰሚና አጋር ለማግኘት መታገል እጅግ ፈታኝ ነበር። ምንም እንኳ አምርሮ በሚታገልና በሚያታግል አመራር የማያቋርጥ ጥረትና ብርቱ ትግል አማካኝነት በሁለቱም ዘርፎች አኩሪ ውጤት ቢገኝም የትግሉን በተጠበቀው ፍጥነት እንዳይጓዝ ማድረጉና የአመራሩንም ህልውና የተፈታተነ ሂደት ነበር።

 

  1. በሶስተኛነት የሚጠቀሰው አብይ ፈተና የገንዘብ እጥረት ነበር። እንደሚታወቀው እያንዳንዷ እንቅስቃሴ የገንዘብ ወጪ አለባት። በተለይም የሃገሪቱን ሃብት ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ገንዘቡን ለስለላና ለመደለያ ከሚያውል ህወሃትን መሰል ድርጃት ጋር መታገል እጅግ ፈታኝ ነበር። ይልቁንም ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን አንድም ጊዜ ከህዝብ የሰበሰበው ወይም ከድርጅት የተደጎመው ምንም አይነት ገንዘብ ሳይኖር ከአባላት ብቻ በሚሰበሰብ ገንዘብ ትግሉን መምራት ተአምር የሚታይ ነበር (የጎንደር አመፅ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በሁለት ድርጅቶች የታቀፉ ወገኖቻችን በራሳቸው ተነሳሽነት ለልሳነ ግፉዓን ገንዘብ እንደለገሱ ማስታወስ እወዳለሁ። በዚህ አጋጥሚ ለወገኖቼ ምስጋናዬ ይድረሳቸው። ስማቸውን ድርጅቱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ይገልፃል ብየ አምናለሁ) ። አንዳንዴም አመራሩ አባላትን ገንዘብ ለመጠየቅ በመሳቀቅ ለአንዳንድ አስቸኳይ ጉዳዮች ከኪሱ የሚያወጣው ገንዘብ ትግሉን በእጅጉ ይፈታተነው እንደነበር ህያው ምስክር ነኝ። ይህን መሰል የገንዘብ ችግር ባይኖርና አመራሩ በአቀደው መሰረት ቢጓዝ ኖሮ ድላችን ዛሬ ካስመዘገብነው አንፀባራቂ ድል እጅግ የላቀ ሊሆን ይችል እንደነበር በፍፁም አልጠራጠርም። በዚህ አጋጣሚ በልሳነ ግፉዓንና በአመራሩ ተማምነው ገንዘባቸውን በተጠየቁ ቁጥር ያለስስት በልግስና በመስጠት ከጎናችን ለተሰለፉ አባሎቻችን ሁሉ ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ። ያለ እናንተ እርዳት ህወሃትን ድል ማድረግ የማይታሰብ ነበርና ነው።

 

  1. በአራተኛነት ደረጃ የሚቀመጠው ወደ ህዝባችን የምንደርስበትና ሃሳባችንን የምናስተላልፍበት የብዙሃን የመገናኛ ዘዴ ማገኘት አለመቻል ነበር። በተለይም ኢሳት እስኪቋቋምና ሙሉ ለሙሉ ከእኛ ጋር መስራት እስኪጀምር ድረስ ወደ ሃገር ቤት የሚገቡት የሬድዮ ስርጭቶች የጀርመንና የአሜሪካ ድምፅ ብቻ በመሆናቸውና የእነሱንም ልብ አሸንፎ መድረኩን ማገኘት እጅግ ፈታኝ ነበር። ወልቃይት ጠግዴና ጠለምትን አስመልክቶ በጀርመን ድምፅ በኩል አልፎ አልፎ ጋዜጠኛ ተክሌ የኋላ ይሰራቸው ከነበሩት ፕሮግራሞች በቀር ጉዳዩ የሚነሳበት ይህ ነው የሚባል እድል አልነበረም። ምንም እንኳ ልሳነ ዓፉዓንም እንደ ድርጅት መድረኩን ለማገኘት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም እድሉን ያገኘበት ወቅት አልነበረም። በዚህም ምክንያት ኢሳት እስከተቋቋመና አብረን መስራት እስከጀመርን ያለው ጊዜ በእጅጉ የሚያስቆጭ እና የብዙ ንፁሃንን ህይወት ማዳን የምንችለበት ወርቃማ ጊዜ ነበር። ይህ ደግሞ ሁሌም ሲያመን ይኖራል።

 

  1. የመጨራሻው እና ሁሌም አደጋው ገዝፎ የሚታየን የመገናኛ ዘዴ ችግር ነው። እንደሚታወቀው የሃገሪቱን የቴሌ አገልግሎት በብቸኝነት ተቆጣጥሩ በዓለም ላይ ውድ በሆኑና በተመሰከረላቸው የስልክ መጥለፊያ ዘዴዎች በመጠቀም ሌት ከቀን የኢትዮጵያን ህዝብ የሚሰልለው ህወሃት ጎንደርን በተለይም በወልቃይት ዙሪያ ከፍተኛ ሃይል አሰማርቶ እንደሚሰራ እንገምት ነበር። በዚህም ምክንያት ወደ ሃገር ቤት የሚደረገው ግንኙነት እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት በመሆኑ ግንኙነቱን ጠባብ፣ የትግሉንም ሂደት አዝጋሚ ሊያደርግው የግድ ነበር። ምንም እንኳ ድርጃታችን በወሰደው ከፍተኛ ጥንቃቄ ምክንያት አንድም መረጃና ተልዕኮ በህወሃት እጅ መግባትና መደናቀፍ ያላጋጠመው ቢሆንም ሂደቱ ግን በተወሰነም ደረጃ ቢሆን መጓተቱ አልቀረም ነበር። የመገናኛው ዘዴ የተሳለጠ ቢሆን ኖሮ ህወሃት አሁን የደረስበትን ሃገር አቀፍ ሽንፈትና ኪሳራ ከ5 ዓመታት በፊት ማስተናገድ በተገደደ ነበር። ይህ ደግሞ የህዝባችንን የስቃይ ጊዜ በእጅጉ ያራዘመ በመሆኑ ያበሳጫል።

4ኛ. የልሳነ ግፉዓን ወደ ፊት የሚጠብቁት ተግዳሮቶች ምን ምን ናቸው?

ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን በዋናነት ከፊት ለፊቱ የሚጠብቁትን ተግዳሮቶች ሙሉ ለሙሉ ለመገመትና ጠንቅቆ ለማወቅና የብዙ አዋቂዎችና ባለሙያዎች ጥረት የሚጠይቅ ይመስለኛል። ለዚህም ሰነድ መዘጋጀት ዋነኛው ገፊ ምክንያት በዚህ ንኡስ ርዕስ ስር በአባላትና በደጋፊዎቻችን በኩል ሊዳሰሱ የሚችሉ ጭብጦችን ታሳቢ በማድረግ ነው። ነገር ግን ከቀደሙት ልምዶቻችን፣ ከሃገራችን ቀደምት ታሪኮችና፣ ካለንበት ሃጋራዊም ሆነ አለም አቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የሚከተሉትን ተግዳሮቶች በታሳቢነት ማንሳት እወዳለሁ። የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ቡድንና በዙሪያው ያሰለፋቸው ቀደምት ጠላቶቻችንን የሞት ሽረት ትግል እንደተጠበቀ ሆኖ፦

 

ሀ. የትግሉን የእድገት ደረጃ ያገናዘበና የጠላትን አሰላለፍ በተረዳ ሁኔታ ድርጅታዊ መፍትሄ የመስጠት አቅምና ክህሎት ጥያቄ፣

 

ለ. ከሁሉም አቅጣጫ እየጨመረ የሄደውን የአባልነት ጥያቄና የእንተባበር ፍላጎት ሊሸከምና በወቅቱ ትክክለኛ ምላሽ ሊሰጥ   የሚችል አመራር፣ ድርጅታዊ መዋቅርና፣ መሪ ሃይል ማስፈለግ፣

 

ሐ. የወልቃይት፣ የጠገዴና፣ የጠለምት ህዝብ ታሪካዊ ትግልና፣ የተገኘውን ህዝባዊ ድል ነጣቂዎችና የአማራነትና፣ የኢትዮጵያዊነትን ለምድ ለብሰው የሚመጡ የህወሃት ተላላኪዎች ጠለፋ (በትንሹም ቢሆን በተግባር የታዬ)፣

 

መ. ህወሃት ለወልቃይትና አካባቢውን በራስ ገዝ ስም ወይም በፌደራል ስር ወይም አዲስ አከላለል በመጠቀም ታጋዩን ህዝብ በመከፋፈላና ከጎንደር ህዝብ በመነጠል ማዳከምና ትግሉን ይበልጡኑ ማደቀቅ (በእንቅስቃሴ ላይ ያለ) … ወዘተ

5ኛ. ልሳነ ግፉዓን ከዚህ ወደ ዬት? ቀጣዩ የትግል ጉዞና አካሄድ ምን መሆን ይኖርበታል?

ማንኛውም ድርጀት ጊዜውን ጠብቆ እንደተወለደ ሁሉ ጊዜውንም ጠብቆ የማደጉ ጉዳይ አይቀሬ ነው። በዚህ የተፈጥሮ መርህ መሰረት ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን ከተቋቋመበት ግዜ ጀምሮ የቆመላቸውን አላማና ግቦች ከማስካት አንፃር ያሳየው ጉዞና እድገት ከላይ በዝርዝር ለማየት ሞክሪያለሁ።

ልሳነ ግፉዓን እንደስሙ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ማህበረሰብ እውነተኛ ልሳን በመሆን የህዝባችን የሰቆቃና የፍትህ ድምፅ  ከኢትዮጵያ ገጠራማ ቀበሌዎች አስከ አሜሪካው መንግስት ስቴት ዲፓርትመንት ድረስ እንዲደመጥ ለማደረግ ችሏል። ይልቁንም ይህ ህዝባዊ የፍትህ ጥያቄና የሰቆቃ ድምፅ ከመደመጥ አልፎ የብዙዎችን ቁጣ የቀሰቀሰና ለመራር ትግል ያነሳሳ በመሆን የፋሽስቱን የህወሃት ስርዓት ከስር መሰርቱ ለማናጋትና ወደ ማይቀርለት ዘላለማዊና ታሪካዊ ሞት ባልተጠበቀ ፍጥነት እያንደረደረው መሆኑ ስረዳና ስመለከት  ታላቅ ኩራትና ደስታ ይሰማኛል።

የአንድን የህዝብ ክፍል የመብትና የህልውና ጥያቄ በፋና ወጊነት አንግቦ በመነሳት የቀሪውን ህዝብ ሙሉ ድጋፍ ካገኙና ከትግሉ ጎን ካሰለፉ በኋላ ቀጣዩ ሂደት ምን መሆን አለበት ብሎ ቆም ብሎ ማሰብና ማንሰላሰል፣ ብሎም ትግሉን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ በማስተዋል መምራት የግድ አስፈላጊ ይመስለኛል። ከዚህም አንፃር በግሌ ከልሳነ ግፉዓን ጋር ያደረግነውን የትግል ጉዞ ቆምብዬ የማሰቢያ ጊዜ ያገኘሁ ይመስለኛል። በተመሳሳይ መልኩ እንዲህ አይነት ቆም ብሎ የማሰቢያና የማንሰላሰያ እድል ልሳነ ግፉዓን እንደ ድርጀት እንዲሁም አመራሩ እንደ መሪ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል ብዬ በጥብቅ አምናለሁ። ስለዚህ እኔም ባገኘሁት የጥሞና ጊዜ ስለ ትግላችን የወደፊት አቅጣጫ የተረዳኝን ነገሮች ማቅረብ እወዳለሁ።

ዝምታው ወደ ድንዘዛ እንዳያድግ ያሰጋኛል

ልሳነ ግፉዓን ካለው ድርጅታዊ አቅምና የአመራር ክህሎት አንፃር ያስመዘገበው ህዝባዊ ድል እጀግ የሚያኮራና የሚደነቅ ነው። በቀዳሚነት ይዞት የተነሳው ህዝባዊ ጥያቄ ዙርያ ማሰባሰብ የቻለውን የህዝብ ብዛትና አይነት ምን አልባትም በሃገራችን ታሪክ ከተከሰቱት ታላላቅ ህዝባዊ ቁጣዎችና ተቃውሞዎች መካከል አንዱ ለመሆን ያቻለ ይመስለኛል።

ይህን የህዝብ ቁጣና ተቃውሞ በትክክለኛው አቅጣጫና በቁርጠኝነት የሚመራው አካል ካለተገኘ እንደ ቀደሙት ታላላቅ ህዝባዊ ቁጣዎች ሁሉ እንዳይቀለበስ ያሰጋኛል። እንዲሁም ይህ ህዝባዊ ቁጣ እንደ ቀደሙት የኢትዮጵያ አብዮቶች ሁሉ ብዙ እበላ-ባይና ቀልባሾች  በዙሪያው ያሰፈሰፉበት ሆኖ ይሰማኛል። ይህም በተግባር እንደታየው ከወልቃይትን ህዝብ የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ህዝባዊ ቁጣ ተከትሎ ከ10 ያላነሱ “አማራ” ተኮር የብሄር ድርጀቶች እንደ እንጉዳይ መፍላታቸው ለተፈጠረው ውዥንብርና ጠለፋ ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል።

በአንፃሩ ደግሞ ከላይ በቀላሉና ህዝብ በሚያውቃቸውና ምስጢራዊ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮር ለማሳየት እንደሞከርኩት የወልቃይትን ህዝብ የማዳን ትግል ጠፍጥፎ የሰራው ልሳነ ግፉዓን ሆኖ እያለና በምን መንገድና እንዴት ባለ ዘዴ እዚህ እንዳደረሰው ባውቅም፤ ይልቁንም ነገሮችን በስክነት የማየት፣ ከጭብጨባውና፣ ከእዩኝ ባይነት እርቆ ትግሉ ላይ ብቻ አድፍጦ መስራቱን እጅግ የማደንቀውና የማከብረው እርምጃ ቢሆንም እንኳ የተወሰደው የበዛ ዝምታ ግን ሳያሳስበኝ አልቀረም።

የጎንደር የ“ጦርነት አውድማነት” እስከመቼ?

በግልፅ እንደሚታወቀው የየካቲት አብዮት ተብሎ በሚታወሰው ዘመን ነፍጥ ያነሱ ሃይሎች ባደረጓቸው የትጥቅ ትግሎች ውስጥ ዋነኛው ምሽጋቸው፣ የመታገያ ሜዳቸው፣ የቀለብ መሰፈሪያቸውና፣ የታጋይ መመልመያቸው ጎንደር ነበር። በአንፃሩ ደግሞ ህወሃት ኢህአፓንና ለጊዜው ስሙን የረሳሁትን አንድ የትግራይ ድርጅት አስገድዶ ከትግራይ ማስወጣቱና ወደ ጎንደር ማሳደዱ በታሪክ ተዘግቦ ይገኛል። የትግራይን ህዝብ ከተለያዩ ፖለቲካ ድርጅቶች ብዝበዛና የእርስ በርስ ክፍፍል አላቆ ለብቻው የተቆጣጠረው ህወሃት በኋላ ላይ እንደ ኢህአፓ፣ ኢዲዩ፣ ከፍኝና፣ ደርግ ሁሉ ምሽጉን ከትግራይ ወደ ጎንደር በማዛወር በተለይም ማዘዣ ጣቢያውን ከደደቢት ነቅሎ ደጀና (ወልቃይት) ውስጥ ማደረጉ ይታወቃል።

እነዚህ ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጎንደር ውስጥ መመሸጋቸው ባልከፍም ነበር። ለህዝቡም በማሰብ አንድ አይነት ስምምነት አድርገው ህዝቡ ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ መቀነስ በቻሉ ነበር። ነገር ግን እነዚህ እርስ በእርሳቸው የሚጠፋፉ ሃይሎች አባላት የሚመለምሉት በቅርብ ከሚያገኙት የጎንደር ገበሬና ወጣት በመሆኑ ይህንን እንደ ወላጅ እናት መሸሸጊያ የሆናቸውን ህዝብ በተለያየ ድርጅት ውስጥ ሆኖ እርስ በእርሱ እንዲዋጋና እንዲተላለቅ አደረጉት። በተለይም አራቱ ሃይሎች ማለትም ደርግ፣ ኢዲዩ፣ ኢህአፓና፣ ህወሃት/ኢህዴን ዋነኞቹ የነበሩ ሲሆን ጎንደርም ከልጆቿ ደም ጋር የሃገሪቱ ዋነኛ የጦርነት አውድማ እንድትሆን ተፈርዶባት ነበር።

ታሪክ እራሱን ይደግማል እንዲሉ ዛሬ በእኛ ዘመን ይህ ዘግናኝ ትዕይንት ዳግም ጎንደር ላይ ዳዴ እያለ መሆኑን የማይረዳ ጎንደሬ ያለ አይመስለኝም። እውነት ለጎንደር ህዝብ የሚቆረቆር ወገን ካለ ዛሬ ጎንደር ላይ ለመመሸግና የጎንደርን ህዝብ ለተልካሻ ተልኳቸው ጭዳ ለማድረግ ያሰፈሰፉ ሃይሎችን ከወዲሁ በቃችሁ! ማለት አስፈላጊ ይመስለኛል። መቸም ቢሆን በቀደመው ታሪካዊ ፍጅት ገፈት ቀማሾችና በቁስሉም ዛሬ ድረስ የምንሰቃይ ተከታታይ ትውልዶች በህይወት እያለን ዳግም ጎንደርን የጦር አውድማ እንድትሆን መፈቀድ የለበትም። ከዚህ ታሪካዊ ጠባሳ እና ከፊት ለፊታችን ከሚጠብቀን የመድቀቅ አዙሪት በመነሳት ከድርጅታችን የሚጠበቁትን ተቀዳሚ ሚናዎችን ለመጠቆም እወዳለሁ።

ዘመኑን የዋጀ ድርጅታዊ መሪነት

በአጠቃላይ ልሳነ ግፉዓን ከዚህ ቀደም ይዟቸው ከተነሳቸው አበይት አላማዎችና ተልዕኮዎች መካከል ግንባር ቀደሞቹን በአመርቂ ሁኔታ አሳክቷል ብዬ አምናለሁ። ይህንንም በዝርዝር ለማሳየት ሞክሪያለሁ። እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ አሁን ቀጣዩን የትግል ሂደት ከወዲሁ በአግባቡ መተለምና አባላቱንና ደጋፊውን ህዝብ በትክክለኛው አቅጣጫ የመምራት አስፈላጊነት ላይ በፅኑ አምናለሁ። ከነዚህም መካከል፦

1ኛ. ዛሬ የወልቃይትን አጀንዳ ተቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ የተሳውና ከፋሽስቱና ከወራሪው የህወሃት ሃይል ጋር እየተጋደለ ያለው የጎንደር ህዝብ ጭብጨባና ሞቅታ በወለዳቸው ነጣቂዎችና አሻሻጮች እየተዋከበ ይገኛል። ይህን በይፋ ቀስቅሰን ወደ መረረ ትግል ያስገባነውን ህዝብ ከዘመኑ ተኩላዎች ጥቃት መከላከል የግድ ይላል። ለዚህም ድርጅታችን ዘመኑ በሚጠይቀው መጠን እራሱን በማሳደግ /Evolve/ እና ወደ መሪ ፖለትካ ድርጅትነት በማሸጋገር፣ ህዝቡን በታማኝነትና በቁርጠኝነት መምራት የጊዜው አንገብጋቢ ትልዕኮ ነው እላለሁ ፣

2ኛ. ከጎንደር ህብረትና ጎንደር ላይ አተኩረው ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር በቅርበት ተባብሮ በመስራትና በማስተባበር ህወሃት በጎንደር ህዝብ ላይ የሚያደርሰውን የጀምላ ጭፍጨፋ በመመከት ስርዓቱን የማስወገድ ትግል አጠናክሮ መምራት፣

3ኛ. የጎንደርን ህዝብ ተጋድሎ ተከትሎ በአጋርነት በመቆም የህይወት ዋጋ እየከፈለ የሚገኘውን የጎጃምና የአካባቢውን ህዝብ ትግል ልዩ ትኩርት ሰጥቶ መደገፍና ማጠናከር፣

4ኛ. የጎንደርን ህዝብ ተቃውሞ በመደገፍ በህወሃት መራሹ መንግስት ላይ የተቀጣጠለውን  ኢትዮጵያዊና ዓለም ዓቀፍዊ ህዝባዊ ቁጣ በግንባር ቀደምትነት ማስተባበርና መምራት፣

5ኛ. ከኢትዮጵያውያን ድርጅቶች ጋር ይፋዊ ውይይት በማድረግ የሃገራችንን አንድነት፣ ዳር ድንበርና፣ ሉዓላዊነት በሚያስጠብቅና የህዝባችንን ሰላም፣ ደህንነትና፣ መብት በሚያረጋግጥ ሁኔታዎች ላይ አተኩሮ መስራት ናቸው።

እንግዲህ እኔ እንደ አንድ ዜጋና የድርጅት አባል አቅሜ በፈቀደልኝ መጠን ለህዝቤና ለሀገሬ ሊሆን የገባል የምለውን ሃሳብ አቅረብኩ። ይህ ሰነድ በድርጅታችን ውስጥ ጤናማና ገንቢ ውይይት እንዲደረግ ይረዳል የሚል እምነት አለኝ። ከዚህም ውይይት በኋላ ልሳነ ግፉዓን ከቀደመው ይልቅ በርትቶና ገዝፎ መሪ የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ ይወጣል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ።

በመጨረሻም እዚህ ላይ ለቀረቡት ሃሳቦችና ጉዳዮች በሙሉ ሃላፊነቱ የእኔ የአብዩ በለው ጌታሁን ቢሆንም እንደ ማንኛውም ሰው ደካማና በህፀፅ የተሞላሁ በመሆኔ ማንኛውንም ስህተት ቢገኝ በቅንነትና ባለማወቅ የተደረግ በመሆኑ ለተፈጠሩት ስህተቶች ሁሉ በቅድሚያ ይቅርታ እጠይቃለሁ። በፁሁፌ ውስጥ የተወላገደውን ሃስብ አቃንታችሁ፣ የጎደለውን ሞልታችሁ በሙሉና በወንድማዊ ቅንነት የድካሜን ፍሬ ታጣጥሙ ዘንድ በአክብሮት እጋብዛለሁ።

አብዩ በለው ጌታሁን

ሰኔ 2009 ዓ.ም (ኮሎምበስ/ኦሃዮ)

ልሳነግፋዓን ድርጅት በተለያዩ ወቅቶች ያወጣቸው መግለጫዎች ናሙና

  1. የልሣነ ግፉዓን ድርጅት መቋቋምን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ …………………………………. November 26 2009
  2. አቶ አባይ መንግሥቱ ወልቃይትን በሚመለከት ከግንቦት 7 ራድዮ ጋር ያደረጉት ቃለምልልስ……………Dec 1 2009
  3. “To the government & people of Sudan” ለሱዳን መንግሥት የቀረበ አቤቱታ …………………….. Janu 10 2010
  4. የዘር ማጽዳት (Ethnic Cleansing) ዘመቻ፡ በወልቃይትና በጠገዴ ማህበረሰብ ላይ!…………………..March 12 2012
  5. የኢትዮጵያ ገዳማትና ካህናቱ ስለሚደርስባቸው ዘርፈብዙ የመብት ረገጣና የሰበአዊ መብት ጥሰት……April 8 2012
  6. አቶ ጎሹ ገብሩና አቶ ቻላቸው አባይ ከኢሳት ቴሌቪዥን ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ………………………. June 15 2012
  7. የትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ተቃዋሚዎችን በማፈን የኢትዮጵያን የነጻነት ትግል አያስቆምም! …….. Aug 17 2014
  8. አቶ ቻላቸው አባይና እና አቶ ፈረደ በኤስቢስ ቃለ መጠይቅ ………………………………………………………… Dec 14 2015
  9. የደም አፍሳሾች ሸንጎና የህወሃት የዘር ፍጅት አዋጅ በወልቃይት ጠገዴ ላይ ……………………………………Feb 24 2016
  10. ይድረስ ለመላው የአማራ ህዝብ ! የህወሃትን ወረራ በፋሽስት ጣሊያን ሚዛን መዝነው !…………………..May 2 2016
  11. የጎንደር ህዝብ ያከሸፈው የፋሽስቱ ህወሃት ወረራና የአጫፋሪዎቹ ጫጫታ……………………………………. July 20 2016
  12. ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ! ውድ ልጆቻችሁን ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አማራ ክልል እንዳትልኩ!…Sep 21 2016
  13. የህዝባችን ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው በህዝባዊ መንግስት ምስረታ ብቻ ነው!!!……………………………….. Oct 07 2016
  14. ለፋሽስቱ ህወሃትና ግብረ በላዎቹ “አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” “አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” እንዳይሆን !…..Oct 19 2016
  15. ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ ትግል፡ በታላቅ ድል ያሸበረቀና ማይቀለበስ የትውልድ ተቀዳሚ አጀንዳ – Dec 27 2016
  16. የህወሃት ድራማ ተዋናኞች ሆይ!  እጃችሁን ከወልቃይት ላይ አንሱ!………………………………………………Janu 24 2017

ወልቃይትን አስመልክቶ በአባላቱ የቀረቡ ጽሁፎች ናሙና

  1. «ደግሞስ ወደ መንግስት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደሆን ማን ያውቃል? » (ከአብዩ በለው)……Oct 2010
  2. ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር ! የወልቃይትና የጠገዴ ማህበረሰብስ? (ከአብዩ በለው) ………………….. Dec 16 2011
  3. ወልቃይት ጠገዴ ማነው? (አባይ፣ ጎሹ፣ ቻላቸው፣ አብዩ) ……………………………………………………………….Janu 28 16