የአቸናፊዎች ፍትሕ

የአቸናፊዎች ፍትሕ

የ“አሸናፊዎች ፍትህ”ና የወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብ

በአለማችን ሁሉም ማዕዘናት ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ በተለያዩ ዘመናትና ሁኔታዎች በተደረጉ ህልቆ መሳፍርት በሌላቸው ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ማህበራዊና፣ ኢኮኖሚያዊ ትግሎችና ፍትጊያዎች “አሸንፈው” ወደ ስልጣንና የሃይል ማማ ላይ የወጡ “አሸናፊ” ግለሰቦቸ፣ ቡድኖች፣ ወይም ህዝቦች ለ“ተሸናፊው” አካል የሚቸሩት ሁለገብ መሰተንግዶ ወይም “ፍትህ” በአይነቱ፣ በመጠኑም ሆነ በይዘቱ እንደዬ አግባቡ ቢለያይም (መለያየቱ እንደተጠበቀ ቢሆንም) በ“ዓለማቀፋዊ የፍትሃዊነት” መመዘኛዎች የእይታ አድማስ ውስጥ በመካተት ለአይን እንዲሞላና ለባላንጠዎቹም ሆነ ለቀሪው የዓለም ክፍል ተፈላጊውን ሰላምና መረጋጋት እንዲያስገኝ ይቻለው ዘንድ ግን የ“ፍትህ” ሥርአቱና ሂደቱ ቢያንስ በ“ነፃ”ና በ“ገለልተኛ” አካላትና ተቋማት መታገዝ ወይም መከወን እንደሚገባውና አፈፃፀሙም በነዚሁ የ“ፍትህ” ተቋማት ቀጥተኛ ክትትልና ድጋፍ እይታ ስር መውደቅ እንደሚያሻው ያለፉት የታሪክ አዙሪቶቻችን ህያው ምስክርና የማንቂያ ወማስጠንቀቂያ ደወሎች ለመሆን ጉልበት አያንሳቸውምና ስለ“ፍትሃዊው” “ፍትህ” ስንመክር ከታሪካዊ እውነታዎቻችን ላይ መደገፉችን ማረጋገጥ ጠቀሜታው የትየለሌ ይሆናል፡፡

ከዚህም እውነታ ጋር በተያያዘ ለዚህ “ፍትሃዊው” “ፍትህ” ለምንለው ቁምነገር ወሳኝ ባለድርሻ አካላት የምንላቸው የሚበዙ ቢመስለንም ቀዳሚውን በተመለከተ ግን በጥቂቱ ማንሳት ወደድን፡፡ በእኛ መረዳት፤ ቀዳሚው ባለድርሻ/stakeholders/ ወይም በታሪክ አጋጣሚና በወቅታዊ የሃይል አሰላለፍ ለጊዜውም ቢሆን የ“አሸናፊነት”ን ድልን ወይም ገፀ-ባህሪን የተቀዳጀው ክፍል ሲሆን በሁሉም ወገን እንዲኖር ለሚፈለገውና ለሚጠበቀው ለእውነተኛው “ፍትህ”፣ ለዘላቂው “ሰላም”ና፣ ለአስተማማኙ “መረጋጋት” የሚኖረው ቁርጠኝነትና ፅናት እጅግ ወሳኝና ለሂደቱም መሳካት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዝ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ያለበለዚያ በ“ተሸናፊው” ክፍልና በገለልተኛ አካላት ብቻ የሚደረገው “ፍትሃዊነት”ን የማስፈን ፍላጎትና ጥረት ውጤቱ የ“ጅብ እርሻ” የመሆኑ ነገር ሳይታለም የተፈታ ይሆናል የሚል ስጋት በእጅጉ ፡፡

በአንፃሩ ደግሞ በተለይም “አሸናፊው” ቡድን በጊዜያዊነት የተፈጠረውን የሃይል አሳላለፍ የበላይነትና የአቅም መዛባት እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለ“ተሸናፊው” ቡድንና ለራሱ የሚሰጠው “ሚዛኑ”ን የሳተና ወደ አንድ ወገን በእጅጉ ያጋደለ ብያኔ ወይም የ“አሸናፊዎች ፍትህ” የተፈጠረውን እክልና ያለመረጋጋት ለጊዜው ያስወገደና ፀጥ-እረጭ ያሰኝ ይምሰል እንጂ በ“ተሸናፊው” በኩል የሚፈጥረው አንድምታ ወይም ስሜት ግን ለ“በቀል” የሚያበቃ አቅምንና ሃይልን ማጠንከሪያ፣ጊዜን መግዣና፣ የ“አሸናፊው”ን ወገን የ“ተቆረጡ ቀናቶች” መለኪያ መሳሪያ ብቻ በመሆን የሚያገለግሉ ይመስሉናል፡፡ በሌላ ወገንም ቢሆን “አሸናፊው” ሃይል የሄደበትን መንገድ ለምን እንደሄደበት እራሱ ያውቃልና ሁሌም በስጋትና፣ በጥርጣሬ፣ ብሎም ፍርሃቱና እያደርም የአቅሙ ውስንነት በሚፈጥሩት “ቅዠት” ውስጥ ለመኖርና ይህ ቅዠት ለወለደው ፍርሃት ማስተንፈሻ ብሎም “እልባት” ይሆን ዘንድ በ“ተሸናፊው” አካል ላይ በሚወስዳቸው “አላስፈላጊ” የእመቃ እርምጃዎች፣ መዳረሻ ያጡ ግፎችና፣ በደሎች እኒህም ሂደቶች በሚወልዱት የ“አምባገነኖች ስካር” ውስጥ ለመኖርና እያደርም በንፁኃን ደም በጨቀዬው የ“አሸናፊነቱ” “ቆጥ” ላይ እራሱን ሰቅሎና አንቆ ለመኖር የተገደደ ይሆናል፡፡

ስለሆነም ይህን ዘላቂ መፍትሄ የማያመጣውን ወደ አንድ ወገን በእጅጉ የተንጋደደውንና በባለድርሻ አካላት/stakeholders/ መካከል ጤናማ የሆነ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የማያስገኘውን  የ“አሸናፊዎች ፍትህ”  ወደጎን በመግፋት በዘላቂነት በሰላምና በመከባበር አብሮ ለመኖርና (አብሮ መኖር የግድ ከሆነ ማለታችን ነው) ለሌላ ዙር እልቂትና ውድመት ላለመዳረግ በሁሉም ወገኖች አይን ይሁንታና እምነት በተቸራቸው ገለልተኛ የፍትህ አካላት በኩል በሚሰጥ “ፍትሃዊው” “ፍትህ”ና በመተማመንና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አፈፃፀም ወይም ትግበራ ለዘላቂው “ሰላም” የመዳረሻ ለመሆን የግድ የሚሉ ጤናማ ጎዳናዎች ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

በአጠቃላይ ለዛሬ በዚህ ጦማር ከላይ እንደመግቢያ ያነሳነውን የ“ፍትሃዊው” “ፍትህ” እይታና ግንዛቤን መሰረት በማድረግ የ“አሸናፊዎች ፍትህ” ለማን? ከማን? እና እንዴት? የሚሉትን መጠይቆች ከወዲያ ወዲህ በማንከላዎስ በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ማህበረሰብና በትግራዩ ነፃ አውጪ ድርጅት /ህወሃት/ መካከል ያለውን ነባራዊ የአሸናፊነትና የተሸናፊነት እውነታ፣ የተከተለውንና እየተከተለ ያለውን አቅጣጫና፣ ለወደፊት ሊኖር ይገባዋል የምንለውን ባህሪና ቅርፅ ለማስጨበጥ እንታትራለን፡፡ መልካም ምንባብ፡፡

የዛሬው ተረኛ አሸናፊና “ፍትሆቹ”

ከዚህ ቀደም በወራሪው የህወሃት ቡድን በኩል በወልቃይት ጠገዴ ማህበረሰብን ላይ በእቅድና በሃይል የተፈፀመውንና እየተፈፀመ የሚገኘውን አስከፊ የዘር ማፅዳት ወንጀል /Ethnic Cleansing/ በዝርዝር የሚያስረዳና በተጨባጭ የሰነድ ማስረጃዎች የተደገፈ የአቋም መግለጫ በየካቲት 7, 2004 ዓ.ም የዘር ማጽዳት (Ethnic Cleansing) ዘመቻ፡ በወልቃይትና በጠገዴ ማህበረሰብ ላይ!” በሚል ርዕስ ማውጣታችን ይታወቃል፡፡ ይህንንም መግለጫ የሚከተለውን ሊንክ በመጫን ማግኘት ይቻላል፡፡ http://www.ecadforum.com/Amharic/wp-content/uploads/2012/02/EthnicCleansing-Welqaite.pdf?d9c344

በዚህም መሰረት ወያኔ ባለፉት 37 ዓመታት የተገበራቸውንና ቀጣይነታቸው የተረጋገጡ እኩይ እርምጃዎቹ፡

1ኛ. ታሪክን በማወላገድና በማጣመም ወልቃይት ጠገዴንና ጠለምትን ትግሪያዊ የማድረግ

2ኛ. የወልቃይት ጠገዴና የጠለምት ዘር በተቀነባበረ ዘዴ በማፅዳት በትግሪያዊነት የመተካት ሂደቶች ሲሆኑ

እነዚህንም የጥፋት መንገዶች በሂደት የህጋዊነት ወይም የፍትሃዊነት ሽፋን ለመስጠት ዛሬም የትግራይ ነፃ አውጪው ቡድን ሁለት ፍትሃዊነት የጎደላቸውና እስከ አሁን የቆየውን ችግር ወደ ላቀ የግፍ ደረጃ ለማሳደግና ብሎም ችግሩን በመላው የትግራይ ህዝብና በጎንደር ህዝቦች መካከል በሚኖረው የበቀል ይዘት ለማስፋት በማቀድ ቀጣይ እርምጃዎች ወይም በእኛ እምነት ህወሃታዊ የ“አሸናፊነት ፍትህ” በወያኔ አኮፋዳ ውስጥ አድፍጠው በተጠንቀቅና በጥንቃቄ እንደሚጠብቁን በተለያዩ ጊዜያት በወያኔ ቱባ ባለስልጣናት አማካኝነት በግልፅም ሆን በሹክሹክታ ወደ ወገናችን መንደር ሲደርሱ ለማስተዋል ችለናል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ይህን እኩይ አጀንዳ ያረዱን የቀድሞው የወያኔ ም/ጠ/ሚ የነበሩት አቶ አዲሱ ለገሰ ሲሆኑ፡፡ይህም 2000 ዓ.ም ወደ ኮሎምበስ ኦሃዮ በመምጣት ጥቂት የአካባቢውን ተወላጆች እየተሹለኮለኩ ባነጋገሩበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህም ወቅት ከእነዚህ የዋህ ወንድሞች ለቀረበላቸው የ“ዕርስታችንን መልሱልን” መሰረታዊ የማንነት ጥያቄ የሰጡት መልስ ግልፅና ቀጥተኛ ነበር፡፡ ይኸውም “እንደ ስልጢ ህዝብ በህዝበ ውሳኔ/ Referendum/” አንዲሰጣችሁ ጠይቁና በዚያ መንገድ መልስ እንዲያገኝ እንረዳችኃለን የሚል ነበር፡፡

በመሰረቱ አቶ አዲሱ የተነሱበትንና የተጋደሉለትን የኢትዮጵያዊነት ህብር ብሄራዊ ትግልና ድርጅታቸውን /ኢህዴን/ ወደጎን ወርውረው በህወሃት ቡራኬ ያልሆኑትን የአማራነት ካባ ከደረቡና በአማራው ህዝብ ስም “ብአዴን” በሚል የቂጣ ስም የስልጣን ወንበራቸውን ካደላደሉ ጀምሮ እጅግ ብዙ ሃገራዊና ክልላዊ ሸፍጦችን ቢፈፅሙም ይሄኛው ማለትም ህወሃት በሃይልና በማን አለብኝነት የወረረውን ታሪካዊውን የወልቃይት ጠገዴና ጠለምትን አካባቢ በህጋዊነትና በህዝበ ውሳኔ ሽፋን ልክ ኤርትራን ባስገነጠሉበት የደናቁርት መንገድ ዳግም ዕርስታችን የትግራይ አካል ለማድረግ የተሰጣቸው የመጨረሻ የቤት ስራ እንደነበር እንረዳለን፡፡ እንደ ምሳሌና መረጃ ሊያቀረቡት የሞከሩት በአሳፋሪነቱና በአሳዛኝነቱ ዳግም “በህዝበ ውሳኔ” /Referendum/ ስም የመላው የኢትዮጵያን ህዝብ ልብ ያደማው የ“ስልጢ”ን ህዝብ ከወንድሙ ከጉራጌ ህዝብ ጋር ለማጋጨትና ለመለያየት የተኬደበትን የክህደት መንገድ ነበር፡፡

ነገር ግን ምንም እንኳ እርሳቸው በተሰጣቸው ገፀ-ባህሪ መሰረት “አዛኝ ቅቤ አንጓች” በመሆን የተለመደውን የአዞ እንባቸውን በማንባት ጉዳዩን ወደ “ህዝበ ውሳኔ” ለመውሰድ ቢሞክሩም የህወሃትን መሰረታዊ የጥፋት አላማና መሰሪ አካሄድ ከፍጥረቱ ጀምሮ የሚረዳው ኩሩው ወገናችን ከተሰደደበት ድረስ ተከትለውት በመምጣት የቀረበለትን የ“ሁለተኛ ዙር” የሞት ድግስ በመረዳት ሰውዬውን በመጡበት መንገድ አሳፍሮ መልሷቸዋል፡፡

በእኒህ ወኔ ቢስ ግለሰብ በኩል የደረሰን መርዶ ለሁለተኛ ጊዜ ያረጋገጡልን ሌላው የህወሃት መስራችና የእኩዩ የ“ታላቋ ትግራይ” ቅዠት አርቃቂ የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ሲሆኑ ይህንንም ህወሃታዊ ቀጣይ የጥቃት ካርድ እንደተደገሰልን ለኢሳት በሰጡት ቃለመጠይቅ ወቅት “የወልቃይት ህዝብ ችግር እንዴት ይፈታል?” ለሚለው የፍትሃዊነትና ወደተጋረጠብን የዘር ማፅዳት አደጋ ያመላከተ ቀጥተኛ ጥያቄ በመለሱት መልስ “የአንድ ክልል የግዛት ወሰን የመጥበብና የመስፋት ጉዳይ መሆኑንና መፍትሄውም በአንድ ሃገርነት ስር እስከተካተትን ድረስ በቀላሉ በዚያው የሚመለስ” መሆኑን በመግለጥ በሚያሳዝን ሁኔታ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማፅዳት ወንጀል እንደ ተራ የአስተዳደር ችግር በማስመሰል አለባብሰው ለማለፍ ሞክረዋል፡፡

እንግዲህ ይህ በእንዲህ እያለ ነበር ሌላኛው የቀድሞው የህወሃት መከላከያ ሚንስትርና የአሁኑ የመድረክ ሰው አቶ እስዬ አብርሃ እዚህ ሰ/አሜሪካ በምርጫ 2002 ወቅት በመጡበት ጊዜ ይህን የወልቃይት ጠገዴ በደል ያሳሰቧቸው/ያነሱባቸው ውድ ኢትዮጵያውያን ችግሩን እንዴት ሊፈታ እንደሚችል ጥያቄ ባቀረቡላቸው ወቅት ነበር “የህዝበ ውሳኔን / Referendum/” መፍትሄነት ካስቀመጡበት የመዠረጧት፡፡

እንግዲህ ለምሳሌነት የእነዚህን ሶስት ከፍተኛ የወያኔ ነባር አመራሮች አቋምና የ“መፍትሄ ሃሳቦች” አነሳን እንጂ ነገርዬውን በብዙ የበታች ሹማምንት በኩል ጆሮዎቻችን ጠግበውታል፡፡ የሚያሳዝነው ግን ሁሉም ከላይ እንደወረደ የሚቀባበሉትን ስንኝ እንደ ወፏ ያዚሙልን እንጂ ስለ ንድፈ ሃሳቡ ምንነት፣ አፈፃፀሙና፣ እንዲሁም ተያያዥና ተዛማጅ ሁኔታዎች ትንፍሽ አይሉም፡፡ አንዳንዴ ውትወታቸው በሰለቸን ጊዜ  ስለ ሚያላዝኑለት “ሪፈረንደም” አጥብቀን በጠየቅናቸውም ጊዜም ቀጣዩን “ስንኝ” ክፍል ከጡት አባታቸው ከአቶ ስብሃት ወይም ከወዲ ዜናዊ ስላልተዜመላቸው ሊነግሩን አልተቻላቸውም፡፡ አይቻላቸውምም፡፡ የህወሃት በቀቀናዊ ተፈጥሮ በራስ ማሰብን አይፈቅድምና ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን፤ እኛ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ተወላጆች ግን ተሐትን ከስረ-መሰረቷ የምናውቃትና መሰሪ አላማዋንም የምንረዳ በመሆናችን የዚህኛው “ህዝበ ውሳኔ” መነሻና መድረሻ ለቀደመው የዘር ማፅዳት ወንጀል ህጋዊ ሽፋን ለመስጠት የሚደረግ ማሟሟቅ መሆኑን ለአለኝታና ተስፋችን ለሆነው ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ቀደም ሲል ስለ በደላችን የያዘውን ግንዛቤ ለማጠናከር ይረዳን ዘንድ እንደሚከተለው ባጭሩ አስቀምጠናል፡፡

ሴራው እንዲህ ነው፡፡ በቀዳሚነት በስብሃት የቀረበው “ታሪክን በማወላገድ ወልቃይትን መቆጣጠር” የሚለውና ከጅምሩ የከሰረውን እቅድ ተከትሎ ተግባር ላይ የዋለውና እስከ አሁንም እየሰራ የሚገኘው ሁለተኛው “ወልቃይት ጠገዴንና ጠለምትን የማፅዳትና በትግሪያዊነት የመተካት” ወይም /Ethnic Cleansing and Tigrinization/ አረመኔያዊ ዘመቻ ቀጣይ ሁለት ግቦችን ያካትታል፡፡ እነርሱም፡-

3ኛ. “ህዝበ-ውሳኔ” /Referendum/ እና

4ኛ. የ“ራስ-ገዝ” አስተዳደር የሚሉት ሲሆኑ፡፡

እስኪ እኒህን ሁለት ህጋዊነትና ዓለምአቀፋዊ ተቀባይነት ያላቸው የሚመስሉ የጥፋት መንገዶችን አንድ በአንድ በዝርዝር ከነ አፈፃፀማቸው እንያቸው፡፡

እቅድ ሶስት፡ “ህዝበ ውሳኔ” /Referendum/

በመሰረተ ሃሰብ ደረጃ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ እስከዛሬዋ እለት ድረስ በማንነቱ ላይ “ህዝበ ውሳኔ” እንዲሰጥ ማንንም ጠይቆ አያውቅም፡፡ ለወደፊትም አይጠይቅም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም ፍንትው ያለ ግልፅ እውነት!! ይኸውም እኛ የወልቃይት ጠገዴንና ጠለምት ማህበረሰቦች በማንነታችን ላይ ብዥታም ሆን ጥርጣሬ ጭራሹንም የለለብንና “ሲያልፍም የማይነካን” መሆኑ ነው፡፡ ከመጀመሪያውም እኛ በህወሃት ማኒፌስቶ አንድምታ ትግሬዎች ናችሁ ተባለብን እንጂ እኛ ስለ እራሳችን ትግሬዎች ነን አላልንም፡፡ አንልምም፡፡ ምክንያቱም ትግሬዎች ስላልሆንና ልንሆን ስለማንችል ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም እኛ ማንነታችንን በሚመለከት “ህዝበ ውሳኔ” የምንሰጥበት መነሻም ሆነ መድረሻ ምክንያትና ግብ የለንም፡፡ ሊኖረን አይችልም፡፡ ይልቅስ እኛ እያልን ያለነው እጅግ በጣም ቀላልና ግልፅ ነው፡፡ ይኸውም መሬታችንና ማንነታችን ከ1983 ዓ.ም በፊት ወደነበረበት ሁኔታ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይመለስልን፡፡ አራት ነጥብ!!!

እንዳውም ከተናገርን አይቀር ዛሬ እዚችው ርዕስ ስር ጨርሰን እንናገረውና እንወረደው፡፡

በአንድ ወቅት ልክ እንደኛው በማንነታቸው ላይ የዘመተውን ታሪክ አጎልዳፊ ሁሉ ለማኮላሸት የቆረጡት ታላቁ የአፋር አባት ሱልጣን አሊሚራህ “የኢትዮጵያን ባንዲራ እንኳንስ እኛ ግመሎቻችን ያውቁታል” በማለት ለአንዴና ለመጨረሻ ከሃዲውን ሁሉ እንዳደባዩት እኛም

የወልቃይት ጠገዴንና ጠለምትን ዕርስት፣ ድንበርና፣ ማንነት እንኳንስ እኛ

(ማረሻችን ምንሽር ፣

መጎልጎያችን ጓንዴ፣ )? ?

እጅግ ይልቁንም ድንበርተኛችን ተከዜ ፣ ጠንቅቆ ያውቀዋልና እርሱኑ ጠይቁት፡፡ እባካችሁ እነርሱንም አድምጡን ብለናል፡፡ጨረስን፡፡

ነገርግን ተላለኪዎቹ አቶ አዲሱም ሆኑ የማሌሊቱ አቶ ስዬ “ህዝበ ውሳኔ” /Referendum/ መፍትሄ ይሆናችኋል ይሉናል፡፡ በተለይም አቶ ስዬም እንዳለው በ“ሪፈረንደም” የሚፈታ ቀላል ችግር ነው ብለዋል፡፡ ግን “ሪፈረንደም” ለማን? በማን? እንዴት? ለሚሉት ተግዳሮቶች ተገቢና የማያወላዳ መልስ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ (በእነዚህ አበይት ተግዳሮቶች ላይ የእኛን ምላሽ ወደ መጨረሻ ይጠብቁን)

አዎን እውነት ነው ለ“ታላቋ ትግራይ” ምስረታና ለ“ወርቁ የትግራይ” ህዝብ ህልውና እኒህ ለምና ድንግል መሬቶች በእጅጉ ያስፈልጓቸው ይሆናል፡፡ ከዚህ እውነታ አንፃር እስከ ዛሬ በህወሃት በኩል የተሄደባቸው መንገዶች ሁሉ ለዚህ “ውስጠ ወይራ” ለሆነ “ህዝበ ውሳኔ” የተካሄደ መሰናዶ /pre referendum/ ብንለው የተሻለ ይመስለናል፡፡ይኸውም የአካባቢውን የህዝብ ስብጥር ሚዛን /Demography/ በአስተማማኝ ሁኔታ ወደ ትግሪያዊነት በመቀየር አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ትግሪያዊ ማድረግና ታሳቢውን የምርጫ ሂደትና ውጤት ሊያደናቅፉ ይችላሉ ተብሎ የሚታሰቡትን  ሁሉ በማሰር፣ በማሰደድና፣ በመግደል መንገዱን ማለስለስ ነበር፡፡

እንግዲህ በትግራዩ ነፃ አውጪ ቡድን እቅድና አላማ መሰረት እነሆ ጎባጣው ቀንቷል፣ ገደሉ ሞልቷል፣ ሸለቆው ተስተካክሏል፡፡ የቀረው የ“ሶስተኛው” መንገድ መከሰት ብቻ ይመስለናል፡፡ ጭራቃዊው “ህዝበ ውሳኔ”፡፡ ታዲያ በወያኔ መንደር በኩል ትግራይን ነፃ የሚያወጣው “ማኒፌስቶ” በ“ዜሮ” ሳይባዛ “እቅድ ሶስት”ን በህልውናችን ላይ በፍጥነት መተግበር ይኖርበታል የሚል መንደፋደፍ በዝቷል፡፡ ከተቻለ የመተካካቱ ድራማ ለለገሰ የመውጫ ቀዳዳ ከመስጠቱ በፊት፡፡ ታዲያ በዚህ ምርጫ እንደተለመደው የ99.6% ውጤት አይታሰብም፡፡ በፍፁም! እንደ እናት ሃገር ኤርትራ የ99.9% እንጂ፡፡ ቀሪዋ 0.1% ውጤት ቀያቸው ውስጥ ያለ ጧሪና ቀባሪ ለቀሩት ባልቴቶችና ህወሃትን ተሸክመው እዚህ ላደረሱ ወንድሞቻችንና እህታችን በተለይም ለእነ ወ/ሮ አዜብ መስፍን የተተወ “ጆከር” ይሆናል፡፡

ታዲያ ይህ መንገድ ይሳካል አይሳካም ከጊዜ ደጉ ጋር አብረን የምናየው ይሆናል፡፡ ነገር ግን በስንዴ ውስጥ እንክርዳድ አይጠፋም እንዲሉ፡-

  • የዛሬ 60 ዓመት የታሰበው ትግራይን “ነፃ” የማውጣት የቀዳማይ-ወያኔ ቅዠት በልጆቻቸውና በልጅ-ልጆቻቸው በተለይም በህወሃቶች የሃገሪቱን የመሪነት ስልጣን ከያዙ እነሆ ከ20 ዓመታት በኃላ እንኳ ትግራይ አሻፈረኝ “ነፃ” አልወጣም ብላ “በመገገሟ” የትግራይ ነፃ አውጪነትን ታፔላቸው ወደ “ታላቋ ትግራይ” እንዳልተንኳተተ ሁሉ፤ (ምን አልባት ሰሞኑን ስብሃት እንዳለው ማሊያቸውን ወደ የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲነት /Demcratic Party of Tigray (DPT)/ ሊቀይር ቢችልም)
  • ማሌሊት በድንገተኛው የሶሻሊስት ጎራ መፍረስ “ቀኗን እንዳጨለመባት”ሁሉ ፤
  • በኢሳያሳዊ “እብደት” የኤርትራ ማፈንገጥ “ትግራይ- ትግርኝትን” እንዳኮላሸው ሁሉ ፤

ወልቃይት ጠገዴና ጠለምትን የመጠቅለሉ አላማ ቢኮላሽ “ጠርጣራው” የትግራዩ ነፃ አውጪ ቡድን የ“አድጊያዋ”ን የ“እኔ ከሞትኩ…. ” እቅዷን በአራተኛ ደረጃነት ምናምኗ ውስጥ ወሽቃለችና የ“እቅድ ሶስት”ን ጉዳይ እዚህ ላይ እንግታና ወደ“አራተኛው” እንለፍ፡፡

 

 

 

እቅድ አራት፡ የራስ-ገዝ አስተዳደር

እንግዲህ ይህ በአራተኝነትና በመጨረሻነት የተቀመጠው መንገድ ቀደም ሲል የተኬደባቸው ሁለቱ መንገዶች እንዲሁም በታሳቢነት የተዘጋጀው የማጠቃለያው ሶስተኛው መንገድ ካልሰራ በሚል የተቀመጠ የሆዳሞችና የጨለምተኞች መንገድ ነው፡፡ በአጭሩ እንደተለመደው ሁሉ ለ“ታላቋ ትግራይ” ያልሆነ ቀሚስ መሬትና ህዝብ ይበጣጠስ የሚል ይመስለናል፡፡ እርግጥ ነው ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የጎንደር ታሪካዊ አካልና የወልቃይቴዎች፣ የጠገድቼዎችና ፣ የጠለምቶች የዘለዓለም ዕርስት የመሆናቸው እውነታ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የትግራይ አካልና ትግሪያዊ የማድረጉ “የማፅዳትና የመተካት” መንገድ በንፁሃን ወገኖቻችን ውድ ደም የተቆለፈና በጀግና ባለአደራዎቻችን ክቡር አጥንት ለዘለዓለም የታጠረ መሆኑና መዳረሻውም ለማንም ፍንትው ብሎ የሚታይ ታሪካዊ እውነት ሆኗል፡፡

ታዲያ ከላይ የተገለጠው እውነታ በተረጋገጠ መንገድ ለቁንጮዎቹ ሲገለጥላቸውና “እቅድ ሶስት” ከጨዋታ ሲወጣ /Phase out/ የከፋውና ሌላኛው መርዘኛ እቅድ ገበያ ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡ ይኸውም ለወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የ“ራስ ገዝ አስተዳደር” ማጎናፀፍ የሚል፡፡ ድንቄም የ“ራስ ገዝ”! ድንቄም ማጎናፀፍ! እስኪ ይህን የ“አድጊያዋ”ን መንገድ እኛ በተረዳነው መንገድ መጠን ለእርስዎ ለክቡር ኢትዮጵያዊ ወገናችን ለማካፈል እንሞክር፡፡

ዛሬ እነሆ የአካባቢው የህዝብ ስብጥር/Demography/ ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስደፍር ሁኔታ በትግሬነት ተቀይሯል፡፡ ነገ ሌላ ቀን ቢሆንም ወያኔ ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ግን ለታሪክና ለምስክርነት የቀረችን መጠሪያ ስማችን እንኳ ሳትቀር በ“ምዕራብ ትግራይነት” በመተካት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከእናት ሃገራችን ካርታ ላይ የመሰናበቷ ነገር እሙን ነው፡፡ በአለፉት 20 ዓመታት በአካባቢው ተወልደው ያደጉ ወጣቶች ጆሮዋቸውን ቢቆርጧቸውም እንኳ አማርኛ የሚባል ቋንቋ እንዳይሰሙና የጎንደርኛ የሆነን ባህል እንዳያውቁና እንዳይኖሩ ተደርገው አድገዋል፡፡  በዚህ ታሪክና ትውልድ በማይረሳው የጥፋት ጎዳና የሚነጉደው ህወሃት ይህን የህዝብ ሚዛን ለመዛባትና እንደ ትልቅ ስኬት ለመቁጠር የተጠቀመባቸው ፡-

1ኛ. ህወሃት በ“ወርቅ ዘርነት” ፕሮፖጋንዳው ያወራቸውንና በድህነት ወለል የሚማቅቁትን ትግሬዎች ከተለያዩ የትግራይ ክፍሎች ባመጣቸው ህልቆ መሳፍርት ሰፋሪዎች (በነገራችን ላይ ይህቺ መንገድ የቀድሞው የኢራቅ መሪ ሳዳም ሁሴን የኢራቅን ኩርዳውያን ለማጥፋትና በአረባዊነት ለመተካት ከተከተለው የአረባዊነት /Arebization/ ዘመቻ የተቀዳች የትግሪያዊነት/Tigrianization/ ቀጥተኛ ግልባጭ የሆነች እኩይ መርዝ ነች ለንፅፅር አጭር መረጃ እነሆ  http://en.wikipedia.org/wiki/Arabization

2ኛ. ድንግልና ለም መሬታችን በግፍና በማን አለብኝነት በሽልማት መልክ የተቸራቸው “ተቀናሽ” ነባር የህወሃት አባላት፡፡ (በነገራችን ላይ እነዚህ ተቀናሽ ቀደምት የህወሃት ተጋዳላዮች ወደ ተወለዱበትና ያደጉበት የትግራይ ክ/ሃገር ያልተመለሱና በርሃም በነበሩበት ጊዜ ሁሉ ወልቃይትና ጠገዴን ከአማራ ለማስመለስ ደማቸውን እንዲያፈሱና አጥንታቸውን እንዲከሰክሱ ሲቀሰቀሱና ሲዘፈንላቸው አብረውም “አማራ ገዳይ”ን ሲዘፍኑ የነበሩ ሲሆኑ ከፓርቲው ከተቀነሱም በኋላም ቢሆን ከእነ ሙሉ ወታደራዊ ትጥቃቸው በዕርስታችን ላይ የሰፈሩና መሬቱም የመስዋዕትነታቸው ውጤት መሆኑን የሚያምኑ ናቸው)፣

 

3ኛ. እንዲሁም በታላላቆቹ የእርሻ ማሳዎቻችን በሁመራ፣ በአዲጎሹ፤ በመዘጋ ወልቃይትና በመላው ሀገራችን ከሚታፈሰው የሰሊጥ፣ የማሽላና፣ የጥጥ ምርቶች  በተለይም ያለባለቤት በተገኘ ድንግልና ለም መሬት ላይ ከሚገኘው የሃብት “መና” የሰከሩና በዘረፋቸው የታወሩ የዘመኑ “አርሶ አደር” ሚሊየነር ባለሃብቶች ፣

4ኛ. እንዲሁም በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ለወያኔ አላማ መሳካት የማዕዘን ድንጋይ ሆነው ለሚያገለግሉ ምንዱባን ሁሉ ወልቃይት ጠገዴን በባለቤትነት “በራስ ገዝ” ስም አንበሽብሾ ውልቅ ይላል፡፡ እነዚህ ከ1ኛ-4ኛ የተዘረዘሩ ምንዱባን ሁሉ ከባለ ርስቱና ከተወላጁ ህዝባችን ልቀውና ገዝፈው “ወልቃይት ጠገዴ ወይም ሞት!” በማለት ከልጅ ልጅ ለሚተላለፈው መጠላላትና መጠፋፋት ሁነኛ ዋስትና ይሰጣሉ ማለት ነው፡፡ “እኔ ከሞትኩ ….” እንዲሉ፡፡

እንግዲህ ይህ በወገናችን ላይ አስቀድሞ የተፈረደው የ“እኔ ከሞትኩ …” አዲጊያዊ፣ ዘለዓለማዊና፣ ትውልድ ተሻጋሪው የበቀል መንገድ ፤ ወያኔ በሃይልና በማን አለብኝነት በሃገራችን ላይ የጫነው የይስሙላ ህገ-መንግሥት አንቀፅ ……. ስለሚደነግገው የ“ባለቤት አልባው”ና የ“አካባቢውን አስተዳደር” በቀጥታ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ እንዲቆጣጠረውና እንዳሻው አስተዳደሩን የመበተንና የመሾም ሙሉ ስልጣን ስለሚሰጠው የ“ራስ-ገዝ አስተዳደር” ስልጣንና ባህሪ ሳናነሳ መሆኑ ነው፡፡( የዚህን ጠንቀኛና ልጓም አልባ  የአስተዳደር ስርአት ጦስ የእነ አርከበ እቁባይ ለአዲስ አበባ ከንቲባነት ያበቃና ድሬዳዋን ለማንም ዘራፊ መፈንጫነት ያበቃ መሆኑን መመልከት ይቻላል)፡፡ ነገር ግን ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ግን ባለቤት አልባ አልነበሩም፡፡ እይደሉም፡፡ ሊሆኑም አይችሉም፡፡ ምክንያቱስ እኛ ባለዕርስቶቹ እንደታቀደው ፈፅሞ አልፀዳንምና ነው፡፡

ይሁንና እኛ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ተወላጆች ታሪካዊ እውነትና ፅኑ የነፃነት ጥማት ስላለን ብቻ በመራር ትግላችን ይህንን የትግራይ ተስፋፊዎችን ግፍና የህወሃትን በደል እንገታዋለን፡፡ ነገር ግን ይህ የነፃነት ትግላችንና ጥማችን በአጭር ጊዜና በአስተማማኝ መልኩ እውን የሚሆነው ልክ የቀደመ ታሪካችን በደማቁ እንደሚያዘክረው የአባቶቻችንን አኩሪ ታሪካዊ መንገድ ስንከተል እንደሆነም በፅኑ እናምናለን፡፡ እንታመናለን፡፡

ይኸውም ወላጆቻችን፤ አያት ቅድመ አያቶቻችን ከጥንት ጀምሮ ለሃገራቸው ለታለቋ ኢትዮጵያና ለመላው ህዝቦቿ ነፃነትና ለዳር ድንበሯ መከበር፤ ደሙን ከደሙ ቀላቅሎ የቅድስት ሃገሩን ጋራ ሸንተረር ያረሰረሰ፣ አጥንቱን ከአጥንቱ አማግሮ ዳርድንበሩን በጀግንነት ያጠረ ኩሩ ህዝብ ልጆች ነንና ዛሬም እኛ የአባቶቻችን ታማኝና ባለአደራ ልጆቻቸው እንደ ቀደሙት ሁሉ ከመላው ኢትዮጵያዊ ወገናችን ጋር በማበር ይህን ዘመን የወለደውን የታሪክ አሜኬላ የሆነው የህወሃት አገር የማፍረስ፣ ታሪክ የመበረዝና፣ ርስት የመንቀል እኩይ ባንዳዊ አላማ እናኮላሻለን፡፡ ይህንንም መንገድ እንዲህ እንደሚከተለው እንተልማለን፡፡

 

 

 

 

ከኢትዮጵያ ህዝብ የምንጠብቀው እውነተኛው “ፍትህ”

በዛሬው “አሸናፊ” በህወሃት ቡድን በኩል የተሄደበትንና ለወደፊቱ የተደገሱልን እጅግ አሳዛኝና እርባና ቢስ የሆኑትን የመጠፋፋት መንገዶች አበይት ያልናቸውን ብቻ በተወሰነ ደረጃ ለማሳየትና ለወገናችን ትክክለኛውን ግንዛቤ ያስጨብጣሉ በምንለው መልኩ ለማቅረብ ሞክረናል፡፡

እርግጥ ነው “ፍትሃዊውን ፍትህ” ሃገር ከሚያፈርስና ታሪክን ከሚያሳክር ተራ “ሽፈታ” በፍፁም አልጠበቅንም፡፡ አንጠበቅም፡፡ ነገር ግን የተፈፀመብን ግፍና በደል እንዲሁም በቀጣይነት ለሚጠባበቀን የ“ዘር አልባነት” የመዳረሻ አደጋ ለሚመለከተው ሁሉ በተለይም ለ“ፍትሃዊው ፍትህ”ና ለሰው ልጆች የተፈጥሮ “ነፃነት”ና “መብቶች”/Human Rights/ ተግተው ዘብ ለቆሙት ለኢትዮጵያ ህዝብና ለመላው የዓለም ህዝቦች ማሳወቅና ትክክለኛውን መረጃ ማድረስ የግድ ስለሚለን እንዲሁም እኛ ከዛሬው አሸናፊያችን ሳይሆን ከእነዚሁ የፍትህ ባለድርሻዎች የምንጠብቀውን “ፍትሃዊ ፍትህ” ለማሳሰብ ጭምር ይህን ክፍል ፃፍን፡፡

ከሁሉም አስቀድሞ ግን እኛ መናገርና ማሳሰብ /appeal/ ስለሚገባን እንዲህና እንዲያ እንላለን እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ታሪካዊ እውነታና ቀጣዩን ህወሃታዊ ተንኮልና ሴራ አያውቅም ወይም አይረዳም ከሚል ጨለምተኝነት በመነሳት አለመሆኑንና በዚህ በኩል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይያዝብን አደራችን ከፍ ያለ ነው፡፡

ከዚህ በመነሳት እኛ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ማህበረሰቦች በ“ትግራይ ነፃ አውጪ” ቡድን ለተፈፀመብን የዘር ማፅዳት/Ethnic Cleansing/ ወንጀል እውነተኛውን “ፍትህ” ከኢትዮጵያ ህዝብ፣ በሃገራችን ያለውን የግፍ አገዛዝ ለማስወገድ ከሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ከሲቪክ ማህበራትና፣ ከሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ከሚመለከታቸው ሁሉ የምንጠብቅ ሲሆን፤ እኛም (የዚህ ጦማር አቅራቢዎች) ከመላው የአካባቢያችን ተወላጆች ጋር በመምከር በቅርቡ ሊደረግ ይገባዋል የምንላቸውን የ“መፍትሄ ኃሳቦች” የምናሳውቅ ይሆናል፡፡

ከዚህ በመቀጠል ከዓለም ማህበረሰብ የምንሻውን አፋጣኝ ድጋፍና የእርምጃዎች እንደሚከተለው እናቀርባለን ፡፡

ከዓለም ማህበረሰብ የምንጠብቀው “ፍትህ”

በአሁኑ ሰአት ወገናችን ከሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ከዘር ማጥፋት ወንጀል ተከላካይ ተቋማት፣ እንዲሁም ከዓለም ማህበረሰብ ሁሉ ከፍተኛ ድጋፎችን ይሻል፡፡

 

ከሁሉም በቅድሚያ ግን አካባቢው ከፍተኛ ወንጀል የሚፈፀምበትና እስከ አሁንም ድረስ ለማንኛውም ገለልተኛ አካላት ማለትም መንግስታዊ ላልሆኑ የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገር ድርጅቶች፣ ለጋዜጠኞች፣ ለሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች እንዲሁም ለሌሎቹ ዝግ በመሆኑ፡፡ በይበልጥም አካባቢው መቼም ቢሆን ለማንኛውም ገለልተኛ አካል ምርመራና እይታ ክፍት ሆኖ የማያውቅ በመሆኑ ይህ አፈናና ወጥመድ ተሰብሮ፡-

  • የወገናችን በደል ለዓለም ሰላም ወዳድ ህዝቦች እንዲደርስ ለማስቻል፣
  • የተፈፀመውና እየተፈፀመ ያለው ወንጀል በገለልተኛና ነፃ ወገኖች እንዲጣራ ለማድረግ እንዲቻል፣
  • ከጥቃቱ ማምለጫ መንገድ ያጡትን ንፁሃን ወገኖቻችን ለመታደግና እነሱም ዘንድ የሚገኙትን አስፈላጊ መረጃዎችን በወቅቱ ለማግኘት እንዲቻል ይረዳ ዘንድ፣

በመጨረሻም በዓለማችን ላይ እጅግ የከፋው የዘር ማፅዳት ወንጀል ዛሬ በህዝባችን ላይ እየተፈፀመ መሆኑን በተጨባጭ በማጋለጥ ወንጀለኞቹን ለፍርድ ለማቅረብ ይቻላል የሚል ሙሉ ተስፋና እምነት አለን፡፡

 

በመቀጠልም ለአለፉት 32 ዓመታት በእቅድ ተደግፎ ፤ በሙሉ ኃይል፣ ጊዜና፣ ጉልበት ተቀነባብሮ በተስፋፊውና ወራሪው የትግራይ ነፃ አውጪ ቡድን እየተፈፀመብን ያለውን የዘር ማፅዳት ወንጀል ለመግታትና ለዚህ የእብሪተኞች ወንጀል የተዳረገውን ዘራችነን ለማዳን፤ ብሎም የሃገራችን መንግስታዊ ስልጣን በሃይልና በጉልበት በመያዝ ይህን ታሪካዊ ማንነት ያለውን የወልቃይት ጠገዴንና ጠለምትን ዘር አፅድቶና አጥፍቶ በትግሪያዊነት የመተካት ወንጀል በመፈፀምና በማስፈፀም ሌት ከቀን የተጠመደውን ይህንም አለም አጥብቆ የተፀየፈውን እኩይ ድርጊት በዋናነት የሚመሩትን፡-

 

  • አቶ መለስ ዜናዊ (ጠ/ሚኒስትርና የህወሃት ሊቀመንበር)ና አስተዳደሩ፤ ለአለፉት 30 ዓመታት የዘር ማፅዳቱ ወንጀል መሪና አስፈፃሚ በመሆን ፣
  • ወ/ሮ አዜብ መስፍን (ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለቤትና የህወሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባል) ፤ ያላትን መንግስታዊ ስልጣንና ሀላፊነት በመጠቀም አካባቢውን ትግሪያዊ የማድረግ ዘመቻ ማንነቷን በመካድ እውቅና በመስጠት፣ ይህንንም የዘር ማፅዳት ዘመቻ በፊት አውራሪነትበመምራት፣ የአካባቢውን የፓርላማ የተመራጭነት ሽፋን በመጠቀም ሂደቱን እያሳለጠችና ይህን ወንጀል አለም እንዳይደርስበት ከፍተኛ ሽፋን በመስጠትና፣ ማንኛውንም አፈና እያካሄደች የምትገኘ የአካባቢው ተወላጅ በመሆኗ፣
  • ለአለፉት 20 ዓመታት የተፈራረቁት የትግራይ ክልል መስተዳድር መሪዎችና አስተዳደራቸው፤ በወገናችን ላይ የተፈፀመውን የዘር ማፅዳት ዘመቻ በማቀነባበርና በመምራት ዘራችንን በማሰር፣ በማሰደድና፣በመግደል እንዲሁም በትግሪያዊነት የመተካቱን ሂደት/Tigirianaization/ ከትግራይ ነዋሪዎችን በማፍለስና በርስታችን ላይ በማስፈር፣

እንዲሁም በየደረጃው ያሉ ሹማምንትና ግብረ አበሮቻቸውን ለፍርድ ለማቅረብ ወንጀለኞቹም ፍርዳቸውን ያገኙ ዘንድ በምናደርገው መራራ ትግል ከጎናችን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ሁሉ ያደርጉል ዘንድ ነው፡፡

 

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝቦችም እንዲሁ!

 

የካቲት 19, 2004 ዓ.ም