Welkait, Tegede and Tselemt.

የወልቃይት ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊነት – ይገረም አለሙ

የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ መነሳት የጀመረበት ጊዜ ጠያቂዎቹ እንደሚሉት ከወያኔ የሥልጣን ዕድሜ በላይ ነው። ስሙን ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ብሎ፤ ዓላማውን ትግራይን ነጻ ማውጣት አደርጎ የተነሳው ቡድን በለስ ቀንቶት ትግራይን መቆጣጠር ሲችል ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል መስፋፋትን ነው የመረጠው። አንደኛው ምክንያት ማሸነፍ ከተቻለ በትግራይ ሳይወሰኑ ማዕከላዊ ሥልጣን ለመያዝ፤ ሁለተኛው ደግሞ “ነጻ ሊያወጧት የታገሉላትን” ትግራይ ግዛት ለም መሬቶቸን በማጠቃለል ማስፋት ናቸው።

የትግራይ አጎራባጅ የሆኑት ለም የጎንደርና የወሎ ወረዳዎች በወረራ የተያዙት ወያኔ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ሳይደርስ ነው። ይህን ወረራ ዜጎች በዝምታ አልተመለከቱም በእሽታ አልተቀበሉም፤ ነገር ግን ወያኔ አንድም በጡንቻ፣ ሁለትም በሕግ ሽፋን በወሰዳቸው የማሰር፣ የመግደልና የመሰወር ርምጃ ተቃውሞውን ለማዳን ችሎ ነበር።

ነገር ግን የመብት ጥያቄ በጠመንጃ የማያዳፍኑት፣ ግንባር ቀደም ጥያቄ አቅራቢዎችንም በመግደል የማያጠፉት በመሆኑ፤ ይሄው ዛሬ የተዳፈነው ተገልጦ፣ በኃይል የተረገጠ የመሰለው ፈንቅሎ፣ ገለን ቀብረነዋል ያሉት ሕይወት ዘርቶ፣ ህዝቡን በአንድ ደምጽ ለተቃውሞ ያነሳሳ፤ በአንጻሩ ገዢዎችን ያሸበረ ለመሆን በቅቷል።

የጥያቄው መሰረት ወልቃይት ጠገዴ ወደ ትግራይ መካለሉ ሆኖ፤ የጥያቄው አቀራረብ እና የሚሰጠው ምላሽ ግን የተለያየ መልክ እየያዘ ብዙ ዘርፎች አውጥቷል። በጠያቂዎች በኩል ሕገ መንግሥታዊ መብታችንን ነው የጠየቅነው፣ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ምላሽ ይሰጠን፣ በማለት እስከ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤት ሲሉ፤ ተጠያቂዎቹ በአሁኑ ወቅት ምላሽ ያላገኘ የማንነት ጥያቄ የለም፣ የወልቃይት ጥያቄ ፀረ ሕገ መንግሥት ነው ከማለት አልፈው፤ ጥያቄውን ለማዳፈን የኃይል ርምጃ መውሰድን ነው የመረጡት። ሕገ መንግሥታዊ የመብት ጥያቄ ሲቀርብ ትክክል ነው ብሎ ምላሽ ለመስጠትም ሆነ፤ ሕገ ወጥ ነው ለማለት ጠመንጃ ማንሳት ሳይሆን ሕገ መንግሥቱን መሰረት ማድረግ ነበር የሚገባው።

ስለፌዴራል አከላለል የሚገልጸው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 46/1 “ክልሎች የሚዋቀሩት በህዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመስረት ነው፣” ይላል። በተገለጹት መስፈርቶች መካከል እና ወይም የሚል ቃል ባለመኖሩ፤ አለበለዛም እነዚህን ባገናዘበ መልኩ ተብሎ ባለመገለጹ፤ ክልሎች ሲዋቀሩ አራቱም መስፈርቶች በሥራ ላይ መዋል ይኖርባቸዋል። ነገር ግን አሁን ያለው አከላለል የተሰራው እነዚህን መስፈርቶች ባሟላ ሳይሆን፤ የህወሓትን ፍላጎት ባማከለ ሁኔታ ነው። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ መስፈርቶቹን በሙሉ ሥራ ላይ ማዋል እንደማይቻል የክልሎችን ይዘት በአንክሮ ማየት ብቻ ይበቃል።

የወልቃይትን ጥያቄ ከዚህ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ አንጻር ሲታይ፤

በሕገ መንግሥቱ የሰፈሩት አራት መስፈርቶች ተግባራዊ አለመሆናቸውን በተናጠል እንያቸው፤

በህዝብ አሰፋፈር፤

አሰፋፈር ሲባል ሰፋሪውን ሰውና የሚሰፈርበትን መሬት ይመለከታል። ከዚህ አንጻር ሕገ መንግሥቱ ወደ ወጣበት 1987 ተመልሰን የወልቃይት ጠገዴን አካባቢ አሰፋፈር ስናስታውስ የምናገኘው የነዋሪውም ሆነ የመሬቱ አሰፋፈር ቤጌምድር ጎንደር እንደነበረ ነው። የመሬቱ አቀማመጥም ሆነ የአካባቢው ሕብረተሰብ ባህል፣ ሥነ-ልቦና፣ ትስስር ወዘተ ከትግራይ ይልቅ ለትናንቱ ጎንደር ለዛሬው አማራ ሚዛን ይደፋል። የወልቃይትን ወደ ትግራይ መከለል የሚቃወሙ ወገኖች የሚያቀርቡትና ተቃውሞውን የሚቃወሙት ወገኖች በማስረጃ ሊቋቋሙት ያልቻሉት በኢትያጵያ ታሪክ ትግሬ ሰው እንጂ፤ ትግራይ መሬቱ ተከዜን ተሻግሮ አያውቅም የሚለው መከራከሪያ የህዝቡን የቀደመ አሰፋፈር እንዴትነት የሚያሳይ ነው። በተለያየ መንገድና ሁኔታ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የሚደረግ ሰፈራ አካባቢውን የእኔ ለማለት አያበቃም።

በሕገ መንግሥቱ የተገለጹትን መስፈርቶች ባላሟላ መልኩ ወልቃይት ወደ ትግራይ መስተዳድር ከተጠቃለለ በኋላ፤ በርካታ የትግራይ ተወላጆች በአካባቢው እንዲሰፍሩ የተደረገው የህዝቡን አሰፋፈር ቅድመ ይዘት በመለወጥ የሚነሳውን ጥያቄ ለመከላከል መሆኑ ግልጽ ነው። የወልቃይት ጉዳይ በህዝበ ውሳኔ አይፈታም የሚለው መከራከሪያ የሚነሳውም ሕገ መንግሥቱ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ በኃይል በተካሄደ ሰፈራ፤ ከነዋሪዎቹ ሰፋሪዎቹ እንዲበልጡ በመደረጉ ነው።

ቋንቋ፤

ይህ መስፈርት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አከላል አብይ መገለጫ ነው። ይሁን እንጂ በሕገ መንግሥቱ የተገለጹ መስፈርቶች እስከመኖራቸው ተርስተው ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ይባል እንጂ፤ አከላለሉ ይህንንም ያሟላ ላለመሆኑ የደቡብ ክልልን ማየት ብቻ ይበቃል። ደቡብ የሚባል ቋንቋም ሆነ “ብሔር ብሔረሰብ ህዝብ” የለም። ወልቃይት ላይ ስንመለስም የአካባቢው ሰዎች እንደሚናገሩት፣ ሌሎችም የምርምርም ሆነ የዓይን ምስክርነት ሲሰጡ እንደሚሰሙት፤ በአካባቢው አማርኛ፣ ትግረኛ እና ዐረብኛ (በእኩል ደረጃም ባይሆን) ይነገራሉ። ይህ ከሆነ አንድን ሦስት ቋንቋ የሚናገር ሰው የግድ ወደ አንድ ብሔር ማስጠጋት ሲፈለግ ከግለሰቡ ምርጫ ውጪ በሌላ ኃይል ሊወሰን አይችልም። ፈቃድ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ የተገለጸ አንድ መስፈርት ነው። የዚህ አብይ ችግር ደግሞ አማራ ትግሬ የሚባል ክልል መፈጠሩ ነው።

ማንነት፣

የሰዎች የማንነት መታወቂያቸው ብሔራቸው/ጎሣቸው፣ የብሔሩ መለያ ደግሞ ቋንቋ በሆነበት ሥርዓት፤ እንደ ወልቃይቴ ያለ ከአንድ በላይ ቋንቋ የሚናገር ማኅበረሰብ ያለ ፈቃዱና ፍላጎቱ ቋንቋውን ስለመናገሩ ብቻ የዚህኛው ወይንም የዛኛው ብሔር ነህ ተብሎ ሲጫንበት፤ አድራጎቱ የጉልበት እንጂ የሕግ አይሆንም። በጉልበት የተፈጸመ ነገር ደግሞ ተግባራዊ ሆኖ የሚቆየው ገዢው ጠንካራ፣ ተገዢው ደካማ እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው። ለሁሉም ግዜ አለውና ነገሮች ሲለወጡ ጥያቄው እንዲህ ፈታኝ ይሆናል።

ትግረኛ መናገራችን ብቻ ትግሬ አያደረገንም የሚሉት ተከራካሪዎች፤ በደስታ ግዜ የምንዘፍነው፣ በኀዘን ግዜ የምናለቅሰው፣ በስር ቋንቋችን በአማርኛ ነው። ወግ ባህላችን፣ አሰራር ልምዳችን የአማራ እንጂ የትግሬ አይደለም ይላሉ። ከዚህ አለፍ ብለውም ወያኔ የፈለገው እኛን ሰዎቹን ሳይሆን ለም መሬታችንን ነው። መሬታችንን የትግራይ ለማድረግ ነው የግድ ትግሬ ሁኑ የተባልነው በማለት ክርክራቸውን ያጠናክራሉ። የፌዴራል አከላለሉ ዜጎችን በብሔር/ጎሣ የማይከፋፍል ቢሆንና የክልሎቹ መጠሪያም በብሔር/ጎሣ ባይሆን፤ ይህ ጥያቄ ባልተነሳ ነበር። በጎሣ/በብሔር ስም የሚጠራ ክልል ፈጥሮ ከፈቃቸዳው ውጪ የዜጎች ማንነት በባለሥልጣኖች ተወስኖ፤ አንተ አማራ ነህ፣ አንተ ትግሬ ነህ፣ … ወዘተ ማለት ቢዘገይም የሚያስገኘው ውጤት እየታየ ነው።

ፈቃድ፤

ለፌዴራል አከላለል ፈቃድ አንዱ መስፈርት ሆኖ ቢገለጽም፤ የአፈጻጸሙ እንዴትነት ግልጽ አይደለም። ፈቃድ የሚጠየቀው ማነው? እንዴት ነው የሚጠየቀውስ? ጠያቂውስ ክልሉ ወይንስ ፌዴራል መንግሥቱ? ክልል ነው ቢባል በሁለት ክልሎች መካከል ያለ የወልቃይት አይነቱ ጉዳይ እንዴት ይሆናል? ፈቃድ የሚለው መስፈርት ያልተብራራ በመሆኑ አፈጻጸሙ እንዴትም ይሁን በማን፤ የአካባቢው ነዋሪ ፈቃደኝነት የማይታለፍ እንደውም ወሳኙ መስፈርት ነው። በሕገ መንግሥቱ የተገለጹት ሦስት መስፈርቶች ተሟልተው የማይገኙ በመሆናቸው የነዋሪውን ፈቃድ መጠየቅ፤ ሌሎቹን ጉድለቶች ሁሉ ያሟላል፣ ይሸፍናል። ነገር ግን ገዢዎች በህዝብ ፈቃድ ፍላጎታችንን አናሳካም ብለው ገና ሳይሞክሩት ስለሚፈሩት ተግባራዊ አያደርጉትም። ተግባራዊ የማያደርጉትን ለምን ሕገ መንግሥት ውስጥ ይጽፋሉ የሚል ጥያቄ ማንሳት ስለ ገዢዎች አለማወቅ ይሆናል።

በጥቅሉ በሀገራችን የተከናወነው የፌዴራል አከላለል ሌሎች ችግሮቹ እንደተጠበቁ ሆነው በሕገ መንግሥቱ የሰፈሩትን መስፈርቶች እንኳን ያላሟላ ነው። በዚህ መልኩ የተሠራውና ክልሎችን በብሔር/ብሔረሰብ ስም እንዲጠሩ ያደረገው ፌዴራላዊ አከላለል (ደቡብ የሚባል ብሔርም ብሔረሰብም ህዝብም አለመኖሩን ልብ ይሏል) ትግራይና አማራ የተባሉትን ክልሎች ለመለየት የሄደበት መንገድ መሬቱን እንጂ ነዋሪውን ያላማከለ፣ የወያኔን ፍላጎት እንጂ ሕገ መንግሥቱን መሰረት ያላደረገ በመሆኑ ነው፤ ጥያቄው ከላይ በመጠኑ ለማሳየት እንደተሞከረው አንዱንም የሕገ መንግሥቱን መስፈርቶች አልተከተለም። ለዓመታት ያላባራውና አሁን ገንፍሎ የወጣው።

የወልቃይት ችግር እንዴት ይፈታል?

ጥያቄው በተጠያቂዎቹ በኩል የተለያየ ስምና ፍረጃ ቢሰጠውም፤ በዚህ ጽሁፍ ለማሳየት እንደተሞከረው ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ነው። በመሆኑም ትናንት በከላዩ ጉልበተኛነትና በተከላዩ ደካማነት የተፈጠረውን ሕገ መንግሥቱን ያላከበረ አከላለል፤ በሕገ መንግሥቱ የሰፈሩትን አራት መስፈርቶች ባገናዘበ ሁኔታ ማስተካከል አንዱ መፍትሔ ነው። ይህ ደግሞ ለወያኔ አንድም ሽንፈት፤ ሁለትም ለትግራይ ትልቅ የኢኮኖሚ መሰረት የሆኑ ቦታዎችን ማጣት ስለሚሆን፤ ተግባራዊነቱ አይታሰቤ ነው።

ሁለተኛው መፍትሔ፤ መሬት ላይ ያለውን አከላለል በሚያጸና መልኩ ሕገ መንግሥቱን መቀየር ነው። ይህ ቢሆን ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ አይሠራም የሚለው ለሕገ መንግሥት መሥራት አለመሥራቱ የባለሙያዎችን ምላሽ የሚያሻ ሆኖ፤ ጥያቄው ሕገ መንግሥታዊ ነው የሚለውን ክርክር ያስቀረው ካሆነ በስተቀር፤ የወያኔን ፍላጎት የሚያስቀጥል እንጂ የህዝቡን ጥያቄ የማይመልስ በመሆኑ ፋይዳ አይኖረውም። ስለሆነም መፍትሔው አንድና አንድ ነው። ወያኔዎች ለወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች የሚሰጡት፤ “ይህ ሊሆን የሚችለው በመቃብራችን ላይ ብቻ ነው” የሚሉት ምላሽ ነው በአስተማማኝ ወደ ዴሞክራሲ ሊያደርሰን የሚችለው መፍትሔ። በግልጽ አነጋገር ከአገዛዝ ወደ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መሸጋገር።

Exit mobile version