የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት ከፍተኛ ስቃይ እየተፈጸመባቸው ነው

የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት ከፍተኛ ስቃይ እየተፈጸመባቸው ነው

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 1/2010)

በእስር ላይ የሚገኙት የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት ከፍተኛ ስቃይ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ለፍርድ ቤት ገለጹ።

ችሎት ቀርበው የደረሰባቸውን በደልና ስቃይ የገለጹት የኮሚቴው አባላት በቀል እየተፈጸመብን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በወልቃይት ጉዳይ በአደባባይ አቋማቸውን ያሳወቁትን ዳኛ ዘርአይ ወልደሰበትን በመቃወሜ ከህዳር 26 ጀምሮ ከ2 ወራት በላይ በጨለማ ቤት ታስሬ እገኛለሁ ሲሉ የኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ መብራቱ ጌታሁን ለችሎቱ ገልጸዋል።

በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ይከላከሉ አይከላከሉ የሚል ብይን ለመስጠት ለየካቲት 12/2010 ቀጠሮ ተጠይቋል።

በጎንደር የተካሄደውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ የታሰሩት የወልቃይት አማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት ሁለቱ ሲፈቱ ሌሎቹ አሁንም በእስር ቤት ናቸው።

ጉዳያቸውን ከሚመለከቱት ዳኞች አንደኛው “ወልቃይት የትግራይ ነው”የሚል አቋም ይዘው በአደባባይ የሚናገሩ፣የሚጽፉ በመሆናቸው ትክክለኛ ፍርድ አይሰጡንም በማለት ተቃውሞ ያቀረቡት የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት በእስር ቤት ከፍተኛ ስቃይና በደል እየተፈጸመባቸው መሆኑን ሲገልጹ ዛሬ የመጀመሪያቸው አይደለም።

ሆኖም ህዳር 26/2010 በዋለው ችሎት ተቃውሞ ያቀረቡባቸው ዳኛ ዘርአይ ወልደሰንበት የበቀል በትራቸውን በመሰንዘራቸው የሚደርስባቸው ስቃይ መባባሱን ነው ዛሬ ችሎት ፊት የተናገሩት።

የኮሚቴው አባላት በዳኛው ላይ ተቃውሞ አቅርበው ጉዳያቸው በእሳቸው እንዳይታይ ፍርድ ቤቱን ቢጠይቁም ውድቅ እንደተደረገባቸው የሚታወስ ነው።

ዛሬ በነበረው ችሎት በዳኛ ዘርአይ ላይ ተቃውሞአቸውን ያቀረቡት ተከሳሽ መብራቱ ጌታሁን ከፍተኛ ችግር እንደደረሰባቸው ገልጸዋል።

ዳኛ ዘርአይ ላይ ተቃውሞ ካቀረብኩበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሁለት ወራት በጨለማ እስር ቤት ከተወሰድኩ በኋላ ድብደባ ተፈጽሞብኛል ያሉት አቶ መብራቱ ማዕከላዊ በነበሩ ጊዜ አይናቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

የታሰርኩት ከአእምሮ ህሙማን ጋር ነው በማለትም ስጋታቸውን ለችሎቱ ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቱ ማረሚያ ቤቱን ማዘዝ የማይችል ከሆነ ልወቀውና ያስገባሁትን ማመልከቻ እሰርዛለሁም ብለዋል አቶ መብራቱ።

ከታሰሩት አምስት የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴ አባላት መሃል ሁለቱ ተፈተዋል።

አቶ መብራቱ ጌታሁን ፣አቶ ጌታቸው አደመና አቶ አታላይ ዛፌ ለየካቲት 12 ቀጠሮ የተሰጣቸው ሲሆን ይከላከሉ ወይም አይከላከሉ የሚለው ብይን ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል።

በአማራ ክልል ጎንደር ጉዳያቸው እየታየላቸው ያሉት ሌላው የኮሚቴ አባል ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ የካቲት 9 ቀጠሮ እንዳላቸው ታውቋል።

የደህንነት መስሪያ ቤቱ ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚጠበቅበትን መረጃ እስካሁን ያላቀረበ በመሆኑ ብያኔ ይሰጥበታል የተባለው የየካቲት 9ኙ ቀጠሮ ሊራዘም እንደሚችል ከወዲሁ ግምት እየተሰነዘረ ነው።