ከልሳነ ግፉዓን ድርጂት የተሰጠ መግለጫ

የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ፣ የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ!

የኢትዮጵያ ህዝብ ከሩብ ምእተ አመት በላይ ለገጠመው የጭቆና፣ የምዝበራና፣ የሽብር ዘመን እልባት ለመስጠት ባደረገው መራራ
ትግል የተጎናጸፈው አንፃራዊ ድል ከጅማሮው ተስፍ ሰጪ የሆነና በሂደቱም የለውጥ ፍሬ ማየት ከጀመረን እነሆ ጥቂት ወራትን
አሳለፍን። በዚህም ኢትዮጵያ ሃገራችን እጅ ከወርች ከታሰረችበት የዘረኞች፣ የዘራፊዎችና፣ የጨካኞች አምባገነናዊ የአገዛዝ
ሰንሰለት የመፈታቷና ወደ ፍቅር፣ ወደ አንድነት፣ ወደ እኩልነትና፣ ነፃነት የምታደርገውን ሰላማዊ የድል ጉዞ ብስራት ከሰማንና
ማየት ከጀመርን እነሆ ዘጠና ቀናት ቆጠርን።
ይህ በህዝባችን ልብ ውስጥና በሃገራችን ሰማይ ላይ የሰፈፈው የፍቅር፣ የአንድነትና፣ የእኩልነት መንፈስ መሬት እንዲረግጥና
ለሁላችንም የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ እንዲወጣ በህዝባዊና ዲሞክራሲያዊ መንግስት መመራትና በነፃና ገለልተኛ
የዲሞክራሲና የፍትህ ተቋማት አማካኝነት መታገዝና መጠበቅ አለበት የሚል ፅኑ እምነት አለን።
ይልቁንም ይህ ህዝባችን ለዘመናት የታገለለትና መጠን የሌለው መስዋዕትነት የከፈለለትን የዲሞክራሲያዊና ህዝባዊ መንግስት
ምስረታ ትግል ዳግም በከንቱዎች እንዳይጠለፍና ዛሬም እንዳይኮላሽ የሁሉንም አስተዋይና አርቆ አሳቢ ዜጋ ሙሉ ድጋፍ፣ ቀጥተኛ
ተሳትፎና፣ ያላሰለሰ ርብርቦሽ ያስፈልገዋል ብለን እናምናለን።
በተለይም በአለፉት ግማሽ መእተ አመታት በህዝባችን ጫንቃ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ሰላሙን፣ ፍቅሩን፣ ነጻነቱን፣
አንድነቱንና፣ ብልጽግናውን ሲያጨናግፉ የነበሩ አምባገነናዊና ጨቋኝ ስርዓቶችን ለማስወገድና ለዲሞክራሲያዊና ህዝባዊ መንግስት
ምስረታ ያለ ተስፋ መቁረጥና መንበርከክ ከፊት በመታገልና በማታገል ዛሬ ለደረስንበት የለውጥ ጅማሮ የአቅማችሁን ሁሉ
ያደረጋችሁ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ ጋዜጠኞች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ አክቲቪስቶች፣ ምሁራን፣ … ወዘተ ሁላችሁ
ዛሬ የተጎናጸፍነውን ህዝባዊ ድልና ሃገራችን የጀመረችው የለውጥ መንገድ ዳግም በእኩዮች ሴራ እንዳይጨነግፍና ወደ ጨለማው
የግዞት ዘመናችን እንዳንመለስ ከምንግዜውም በላይ በአንድነትና በፍቅር መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንዘምት ይገባል ብሎ
ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን ያምናል።
ዛሬ በኢትዮጵያ ሃገራችን ውስጥ በጠቅላይ ሚንስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ መሪነት የተጀመረውንና ህዝባችን ወደ ፍቅር፣
አንድነትና፣ ዲሞክራሲ የሚያደርገውን ጉዞ በታላቅ ደስታና በልዩ ስስት እየተከታተልን ሲሆን፣ የፌደራሉና የክልል መንግስታት
ለህዝብ ጥያቄ መልስ ለመስጠት እየወስዷቸው ያሉትን አበረታችና ተስፋ ስጪ የለውጥ እርምጃዎች ላቅ ባለ አክብሮትና አድናቆት
ተመልክተናቸዋል፣ ተቀብለናቸዋል።
ይልቁንም በጠቅላይ ሚንስትር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ በም/ጠቅላይ ሚንስትር በክቡር አቶ ደመቀ መኮነንና በአማራ ክልላዊ መንግስት
ፕሬዘደንት በክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በኩል የቀረበውን ዲሞክርሲን የማበርታትና ለለውጥ የመደመር ሃገራዊ ጥሪና በሃገራችን ውስጥ
የተጀመረውን ወደ ፍቅር፣ ወደ አንድነትና፣ ወደ ሰላም በሚደረገው የለውጥ ጉዞ ውስጥ በንቃት ለመሳተፍና ለማገዝ የሚያስችለን ሆኖ
የቀርበልንን የ”አብረን እንስራ” ወገናዊ ግብዣ ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን በታላቅ አክብሮትና ትህትና ተቀብሎታል።
ከሁሉም አስቀድሞ ዛሬ ለኢትዮጵያ ሀገራችን አንድነት፣ ሉዓላዊነት መጠበቅ፣ ለህዝባችን ሰላምና ፍቅር መስፈን የቀረበውን
ሃገራዊና ክልላዊ የመደመር ጥሪ ስንቀበልና የድርጅታችን ከፍተኛ አመራሮች የያዘ የልኡካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ስንልክ፤ ትላንት
ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ” ብሎ የጀመረውን ፍትሃዊ የህልውና ትግል ተቀላቅለው በፅናትና
በቁርጠኝነት ከጎናችን በመቆም ዛሬ በሃገራችን ኢትዮጵያ ለሚታየው የለውጥ ሂደትና ህዝባችን ለተጎናጸፋቸው ተስፋ ሰጪ ጅምር
ድሎች መገኘት ውድ ህይወታቸውንና ክቡር አካላቸውን ለሰዉ ወገኖቻችን ያለንን አክብሮትና ምስጋና በማቅረብ ነው።
ሰለሆነም ዛሬ ልሳነ ግፉዓን ወደ ሃገር ቤት ገብቶ ለመታገል ሲወስን መስዋዕትነታችሁ ፍሬ አፍርቶና እናንተ የተሰዋችሁለት
የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ ህልውና የመታደግና ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የማሸጋገር ታሪካዊ ጉዞ በድል
ተጠናቆ መስዋዕትነታችሁ ለዘለዓለም በትውልድ ልብና በታሪካችን ውስጥ ነግሶ በዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ውስጥ በመንፈስ
ህያው ሆናችሁ የምትኖሩበት ዘመን እንዲመጣ ከምንግዜውም በላይ በርትተንና ጸንተን ለመታገል ቃል በመግባት ጭምር ሲሆን፣
1ኛ. በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ ላይ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ድርጅት የፈጸመውን የዘር ማፅዳትና አማራዊ ማንነቱን
የማጥፋት አኩይ ሴራና ወንጀል በማጋለጥና በመከላከል ላይ በማተኮር አማራዊ ዘራችን ከጥፋት ለመታደግ የምናደርገውን ትግል
አጠናክሮ ለመቀጠል፣
2ኛ. የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ድርጅት ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ በሃይል የወረራቸውንና በሂደት ወደ ትግራይ የከለላቸውንና
በኋላም ህወሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በቋቋመው ቋንቋን/ብሔርን መሰረት ያደረገ ፌደራላዊ
ስርዓት ሽፋን ያለ ህዝባችን ፈቃድና ይሁንታ በይፋና በማን አለብኝነት ወደ ትግራይ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር ስር የከለላቸውን
የወልቃይት የጠገዴና የጠለምት ለም መሬቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ቀደመው የጎንደር አስተዳደር ወይም የአሁኑ የአማራ
ክልላዊ መንግስት የአስተዳደር ስርዓት ውስጥ እንዲካለሉ ለማስቻል ምናደርገውን ትግል ለማጠናከርና ለማሳካት፣
3ኛ. በአጠቃላይ ዛሬ የወልቃይት ህዝብ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ድርጅት በከፈተበት የታቀደና የተቀነባበረ ወረራና የዘር ማፅዳት
ጥቃት ከትውልድ ቀዬውና ከአባቶቹ እርስት በግፍ ተነቅሎና አማራዊ ዘሩን ከፍፅሞ ጥፋት ለማዳን ሲል በየአቅጣጫው ተሰዶ በብዙ
እንግልትና መባዘን ላይ እንደሚገኝ የአደባባይ ምስጢር ነው። ስለሆነም በሃገር ቤት ውስጥ በተለይም በጎንደርና በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች
ተበታትኖ የሚገኘውን ጀግና እና ኩሩ ኢትዮጵያዊ ወገናችንን በአካል በማግኘት ዛሬ የገጠመውን የህልውና አደጋ መክቶና በድል አድራጊነት
ተወጥቶ እንደ ቀደሙት አባቶቹ በኢትዮጵያ ሃገራዊ አንድነት ግንባታ፣ ለህዝቧ ሰላምና ፍቅር መስፈን ፣ እንዲሁም በተጀመረው
የዲሞክራሲያዊና ህዝባዊ መንግስት ምስረታ ሂደት ላይ ሊያበረክት በሚችላቸው ገንቢ አስተዋፅዖዎች ላይ
ለመመካከርና ብሎም አብሮ ለመስራት ከፍተኛ የድርጅታችንን አመራሮች ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ወስኗል።
በመጨርሻም ሃገራችን ኢትዮጵያ ሁሉም መልካም ነገር ሞልቶ የተትረፈረፈባትና የልጆች ሃብታም የሆነች ቅድስት ሃገር ናት።
ኢትዮጵያ ለሁላችን በእኩልነት ልትለግሰን የሚያስችል የተፈጥሮ ሃብትና ጸጋ ያላት ሃብታም ቤታችን ናት። ህዝባችን ከፍቅር፣
ከሰላምና፣ ከአንድነት ውጭ የሚስማማው ምንም ነገር እንደሌለ በሃይል ረግጠውና ከፋፍለው ሊገዙት የሞከሩትን ወራሪዎችና
አምባገነን መንግስታት ደጋግሞ እንዳሸነፋቸውና እራሱን ነፃ እንዳወጣ ታሪክ ህያው ምስክር ነው። ዛሬም ህዝባችን በመራራ ትግሉና
በክቡር መስዋዕትነቱ የተጎናጸፈውን አንፃራዊ ሰላምና ያስጀመረውን የለውጥ ጉዞ ሃገር ቤት ውስጥ በመግባትና በአካል ህዝባችን
መካከል በመገኘት በሙሉ አቅማችን ለማገዝና ለተሻለ ውጤት ለማብቃት እንደምንሰራ ለምንወደውና ለምናከብረው ህዝባችን
ቃል በመግባት ነው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቧን ለዘለዓለም ይባርክ!
ድል ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት!
ድል ለህዝባችን ፍቅርና ሰላም!
ልሳነ ግፉዓን ድርጅት
ሐምሌ 5, 2010 ዓ.ም
ኦሃዮ/ሰሜን አሜሪካ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*