‘ልሳነ ግፉአን’ የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ አዲስ አበባ ገብቷል _ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

https://www.ena.et/?p=9846

‘ልሳነ ግፉአን’ የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ አዲስ አበባ ገብቷል

አዲስ አበባ ሐምሌ 5/2010 መቀመጫውን ሰሜን አሜሪካን አድርጎ ለ16 ዓመታት በኢትዮጵያዊያን ሰብዓዊ መብት ዙሪያ ሲንቀሳቀስ የነበረው ‘ልሳነ ግፉአን’ የተሰኘው ድርጅት ኃላፊዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።

ድርጅቱ የኢትዮጵያዊያን መብት መነፈግን መነሻ በማድረግ በመሟገት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የድርጅቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ሶስት ወራት በአገሪቱ እጅግ ተስፋ ሰጪና ምቹ ሁኔታዎች በመመቻቸቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ወስኗል።

የ’ልሳነ ግፉአን’ ሊቀመንበር አቶ አብዩ በለው ጌታሁን እንዳሉት ድርጅቱ ሙሉ ትኩረቱ ድምጽ ለሌላቸው የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ማህበረሰብ ድምጽ ለመሆን ዓልሞ የተቋቋመ ነበር።

ሊቀመንበሩ የወልቃይት ማህበረሰብ መብቱን ተነፍጓል፣ ነጻነት አጥቷል የሚል ዕምነትና ይህም በመረጃ የተደገፈ በመሆኑ ለህዝቡ ልሳን ለመሆን ከአገር ውጪ ሆነን ትግል ጀምረን ነበር ብለዋል።

“በዚህ ወቅት በአገሪቷ ተስፋ ሰጪና የተመቻቸ ሁኔታ ተፈጥሯል” የሚል ዕምነት በመያዝ በአገርና ሕዝብ መሓል ሆነው በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ለመታገል መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ሌላው የደርጅቱ መሪ አቶ ገብሩ ማማድ በበኩላቸው አሁን እየተካሄደ ያለውን አገራዊ ለውጥ ማገዝ እና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ድርሻውን ሊወጣና ወደ ተግባር ተግባር እንዲቀይረው ጠይቀዋል።

በአገሪቷ ባለፉት ሶስት ወራት በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የተወሰዱ እርምጃዎችም እጅግ የሚያበረታቱ፣ሰላምን የሚያመጡና የኢትዮጵያን አንድነት እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆኑ አጋሮቾቸው በተለይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ፣ አቶ ገዱና አቶ ለማም ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።

እነዚህ ሰዎች የሚያነሷቸው ሃሳቦች ለዘመናት በተቃዋሚ ድርጅቶች ጎራ ሲነሱ የነበሩ ሲሆኑ አሁን ደግሞ በመንግስት በኩል እየተነሱና እየተስተናገዱ መሆናቸው ጥሩ ለውጥ ነው ብለዋል።

ሕዝቡ እስካሁን በትግሉ ያረጋገጣቸው ድሎች አየር ላይ እንዳይቀሩ ጥያቄዎቹ መመለሳቸውን የሚያረጋግጥበት ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ መስራት ያስልጋልም ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦችን ግንኙነት ለማደስ የተደረገው እንቅስቃሴና የተገኘው ውጤትም የሚደገፍና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያስደሰተ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሌሎች በተለያዩ አገራት የሚገኙ ድርጅቶችም ለውጡን በመደገፍ በሰከነ መንፈስ ወቅቱን የጠበቀ ውሳኔ ላይ ደርሰው የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪያቸውን አስተላልዋል።