ከልሳነ ግፉዓን ድርጅት የተሰጠ የሐዘን መግለጫ

 

ከልሳነ ግፉዓን ድርጅት የተሰጠ የሃዘን መግለጫ

ኢትዮጵያ ሃገራችን ወደ ሰላምና ዲሞክራሲ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ ከጅምሩ ብዙ እንቅፋቶችና ውጣ ውረዶች
የተጋረጡበት እንደሚሆንና የዚህ ሁሉ ችግር መንስኤ ደግሞ በአለፉት 27 የጭቆና እና የግፍ ዘመናት በህዝባችንና
በሃገራችን ላይ የተፈጸሙት እኩይ ተግባራት ድምር ውጤት መሆኑን ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን ይገነዘባል።
ከዚህም በመነሳት የለውጥ ሃይሉ ለአለፈው አንድ አመት የወሰዳቸው አስደናቂ የለውጥ ውሳኔዎችና ተግባራት በእጀጉ
የሚያኮሩና ወደ ምንናፍቀው ሰላምና ዲሞክራሲ ለመጓዝ መንገዱ የተጀመረ ለመሆኑ አመላካች ሆኖ ያገኘነው ሲሆን
በመንገዳችንም ላይ በሚገጥሙን መሰናክሎችና ፈተናዎች ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚያደርጉ ናቸው።
ይሁንና በአለፉት አንድ አመት ውስጥ እንደ አንድ ታላቅ ሃገር፣ ኩሩና ጨዋ ህዝብ ከጋጠሙን መሰናክሎችና ፈተናዎች
መካከል ሰኔ 15, 2011 ዓ.ም ባህርዳር እና አዲስ አበባ ላይ በንጹሃንና ሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸሙት
ግድያዎች እጅግ የከፋ አስደንጋጭና አሳዛኝ ሆኖብናል።
በተለይም የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት አማራ ህዝብ የዘመናት ሰቆቃና ምሬት እንዲያበቃና በፍትሃዊነት እንዲቋጭ
ከጎናችን ተሰልፈው ለመታገል የማይታበይ ቃላቸው የሰጡንና እስከ ህቅታቸው ድረስ በጽናትና በቁርጠኝነት ከጎናችን
የቆሙትን ከፍተኛ የአዴፓ አመራሮች በእንዲህ አይነት ጭካኔና ኢሰብዓዊነት በጎደለው ሁኔታ ማጣታችን ለትውልድ
የሚተርፍ ሃዘን፣ ጸጸትና ቁጭት ጥሎብናል።
ወንድማችን ዶ/ር አምባቸው መኮንን ከለውጡ ጅማሮ አንስቶ እስከ በአጭር በተቀጨው የመሪነት ዘመኑ የወልቃይትን
ህዝብ ጥያቄ "የህልውና ጥያቄ" መሆኑን በመቀበል፣ የህዝባችን ትግል ፍትሃዊ እልባት እንዲያገኝ ከትግላችን ጎን
በመሰለፍ፣ ይልቁንም ፋሽስቱን የትህነግ አመራር በቁርጠኝነት ለመጋፈጥ የሄደበት እርቀትና ያደረገውን መራራ ትግል
ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን በኩራትና በቁጭት የሚመሰክረው ሲሆን ይህም ገድል በወልቃይት ህዝብ የትግል ታሪክ ውስጥ
ለዘለዓለም ሲዘከር ይኖራል።
ኢትዮጵያ ሃገራችን ወደ ሰላምና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የምታደርገው ጉዞ እጅግ አድካሚና እልህ አስጨራሽ
መሆኑን ብናውቅም፤ እንዲሁም ለህዝባችን ህልውና መረጋገጥ የምናደርገው ትግል መራራና ገና ብዙ ዋጋ የሚጠይቅ
መሆኑ ብንረዳም፤ ይልቁንም የትግላችን አጋዥ ወንድሞቻችንና ሃገርንና ህዝብን ወደ ላቀ ደረጃ የማሻገር ሁነኛ ተስፋ
የተጣለባቸውን መሪዎች ፍጹም ኢሰብዓዊነት በጎደለውና ባለተጠበቀ ሁኔታ እስከ ወዲያኛው ብናጣቸውም፤ ድርጅታችን
ልሳነ ግፉዓን ለለውጥ ሃይሉ ያለውን ድጋፍና አጋርነት፣ እንዲሁም በጋራ የምናደርጋቸውን ትግሎች ከምንግዜውም በላቀና
በበሰለ ሁኔታ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ማረጋገጥ ይወዳል።
በመጨረሻም በዚህ መጥፎ አጋጣሚ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን እግዚዓብሔር አምላክ ለነብሳቸው ፍጹም እረፍትን
እንዲሰጥልንና ለመላው ቤተሰቦቻቸው፣ ለስራ ባልደረቦቻቸውና፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ መጽናናትን ይሰጥልን ዘንድ
እንለምናለን።

ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ያፅናናልን

ልሳነ ግፉዓን ድርጅት
ሰኔ 19, 2011 ዓ.ም
ሰሜን አሜሪካ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*