በወቅታዊ የሀገራችን ጉዳይ ላይ ከልሳነ ግፉዓን ድርጅት የተሰጠ መግለጫ

ከጥንቱም ሌባ ሲሸሽ የዘረፈውን እያንጠባጠበና መውሰድ ያቃተውን እያበላሸ ነው!
አበው “ተፈጥሮን ተመክሮ አያድነውም” እንዲሉ የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግንባር /ትህነግ/ በአለፉት 25 ዓመታት የኢትዮጵያን መንግስታዊ ስልጣን በብቸኝነት ከላይ እስከ ታች ይዞ በሃገርና በህዝብ ላይ የፈፀመው አይን ያወጣ ሃገራዊ ሌብነትና ዝርፊያ፣ ህዝባዊ እልቂትና ምስቅልቅል፣ ሃገራዊ ክህደትና ውርደት፣ አጠቃላይ ወንጀልና ሰቆቃ ለመረዳት ዛሬ በመንግስት የዜና ማሰራጫ አውታሮችን ብቻ የሚተላለፉ ምስክርነቶችን መመልከት በቂ ነው።
ይሁን እንጂ ሌባ በባህሪው አልጠግብ ባይና ያገኘውን ሁሉ አግበስባሽ እንደ ሆነው ሁሉ ባለንብረቱ ሲደረስበትና ከመያዝ ለማምለጥ ሲሞክር በስርቆት ያግበሰበሰውን ኮተት አንድ በአንድ እያንጠባጠበ መሸሸቱ የተለመደ ክስተት ሲሆን፣ አቅምና ግዜ ካገኘ መውሰድ ያልቻላቸውን ውድና አስጎምዢ ንብረቶች ባለቤቱ እንዳይጠቀምባቸው በማሰብ ብቻ መሰባበርና ማበላሸት አይነተኛ የሌባ መገለጫ ባህርያት ናቸው።
እናም ሌባውና አልጠግብ ባዩ ትህነግ ከጎንደር ታሪካዊና ለም መሬቶች መካከል ወልቃይትን፣ ጠገዴን፣ ጠለምትን፤ እንዲሁም ከወሎ ራያ-አዘቦን፣ አላማጣን፣ … በግፍና በማን አለብኝነት ሽፍታ እያለ በወረራ ስልጣኑን ሲይዝ ደግሞ በቋንቋ ፌደራሊዝም ሽፋን እንዳሻው ወደ ሚፈነጭባትና ወደ ሚገዛት የትግራይ ሪፐብሊክ የከለላቸው መሆኑ ይታወቃል። አልፎ ተርፎም ራስ-ደጀንን፣ ቤንሻጉልን፣ ጋምቤላን፣ ሱማሌን፣ አፋርን … ወዘተ ሊጠቀልል እያዘናጋ እንደነበረ የመንፈቅ ትዝታ ነው።
በሌላ በኩል “አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ” እንዲሉ በማንነት ድፍጠጣና በዘር ማፅዳት ወንጀል የሚከሰሰው ትህነግ አንዴ “ያለተመለሰ የማንነት ጥያቄ የለም” ይለናል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ “ጥያቄው በትግራይ ክልል በኩል አልቀረበም” ያሰኛል፤ አሁን ደግሞ ከአንደበታቸው የሚወጡ ቃላቶቻቸው እርስ በእርስ ሲጣረሱ እንኳን የማያፍሩትንና ለራሳቸው ክብር የሌላቸውን ወ/ሮ ኬሪያን አይን በጨው አጥቦ የወልቃይትና የራያን “የማንነት ጥያቄዎች” ልፈታ “ገለልተኛ” ኮሚሽን አቋቁሚያለሁ ይለናል።
“የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” እንዲሉ ወ/ሮ ኬሪያ የትህነግ መሪ ሆነውና እርሳቸው የሚመሩት ድርጅት በማንነት ጥያቄና በዘር ማፅዳት ወንጀል ተከሶ እያለ፤ የተከሰሱበትን ወንጀል እኔው እራሴ ካልዳኘሁ በሚል ሚዲያው ሁሉ ላይ ፊጢጥ በማለት ለያዥ ለገራዥ ያስቸገሩ ህሊና ቢስ ሆነው አግኝተናቸዋል።
ወ/ሮ ኬሪያ ለአለፉት ሶስት አመታት በህዝባችን ላይ የፈጸሙት እንግልትና ቧልት አልበቃ ብሏቸው ዛሬም በአንድ በኩል “ገለልተኛ” ኮሚሽን አቋቁማለሁ እያሉ ሚዲያውን የሙጥኝ ብለዋል፣ በሌላ በኩል ደግሞ እጅግ በሚያሳፍርና በሚያስተዛዝብ ሁኔታ ትላንት ጠገዴ ላይ እንዳደረጉት ሁሉ ዛሬም ወልቃይት ላይ ምሽግ ያስቆፍራሉ፣ የአማራን ህዝብ በገፍ ያፈናቅላሉ፣ ሽማግሌና ታዳጊ ህፃናት ሳይቀሩ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ያስታጥቃሉ፣ የጦርነት ነጋሪት ያስጎስማሉ።
ይህ በትህነግ/ወያኔ መንደር የሚደርገው ውዥንብርና ቅብጥርጥር የሚያሳየው ታሪካዊና የማይቀለበሰውን ሽንፈትን ለመሸፋፈንና ወራሪዎቹ ከገቡበት የውርደት አዘቅት ውስጥ መውጫ ቀዳዳ መንገድ ለማግኘት የሚደረገ መላላጥ መሆኑን ብናውቅም ቅሉ ለወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ ግን ትልቅ የድል ጅማሮ መሆኑን ለማብሰር እንገደዳለን። ምክንያቱም፦
1ኛ. ወራሪው ትህነግ ተገዶም ቢሆን ከዘረፋቸው የህዝብና የሃገር ሃብታትና ማንነቶች መካከል ወልቃይትን ለማንጠባጠብ የተገደደ ሲሆን፣ ዛሬ በይፋ ወልቃይት የትግራይ አካል እንዳልሆነና ሊሆን እንደማይችል ለመመስከር እንዳሻው በሚቀልድበት የፌደሬሽን ም/ቤት በር ላይ ከፊት መስመር በተላላኪዎቹ በኩል ተሰልፎ የሚገኝ ሲሆን፤
2ኛ. “ታጥቦ ጭቃ” የሆነው ትህነግ ለ25 ዓመታት የያዘውን የመንግስት ስልጣን በአግባቡ ተጠቅሞ ይህን ታላቅ ሃገርና ኩሩ ህዝብን ለመምራት ካለመቻሉም ባሻገር ሃላፊነቱን ለተራ ሌብነትና ለመንደርተኝነት በማባከኑ ምክንያት በህዝብ ቁጣና በለውጥ ሃይሎች ስልጣኑን ተነጥቆ ከ40 ዓመታት በፊት ወደ ነበረበት ተራ የሽፍትነት፣ የሽብርና፣ የውንብድና ተግባር ተመልሷልና ነው።
ነገር ግን ይህ ለዓለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ስር የሰደደ እኩይ ሴራና የመሬት ቅርምት ዛሬ በህዝብ ያላሰለሰ ተጋድሎ የተገታና የተዘረፉ ዘርፈ ብዙ የህዝብ ሃብቶች ከሌባው እጅ ላይ ለማንጠባጠብ የተቻለ ቢሆንም… ሌባ የሰረቀውን እቃ ባለቤቱ እጅ እንደሚገባ ባወቀ ጊዜ ሊሰብረው ወይም ሊያበላሸው እንደ ሚተጋው ሁሉ ወራሪው ትህነግም የወልቃይትን ህዝብ “ማንነት የለህም” በማለት “ወልቃይት ትግሬም አማራም አይደለም” “ለወልቃይት ራስ ገዝ ይሰጠው” … ወዘተ የሚሉ በማር ሳይሆን በእሬት የተለወሱ የእባብ መርዞች ይዞ ወደ አደባባይ መውጣቱንና እንደ ተለመደው ህዝብን ለመከፋፈልና አካባቢውንም ለማተራመስ እየታተረ መሆኑን አረጋግጠናል።
ነገር ግን ይህ የትህነግ የረጅም ግዜና የመጨረሻው መጨረሻ እኩይ እቅድ አላማ የወልቃይትን ህዝብ ቢቻል ከጎንደርና ከመላው የአማራ ህዝብ ለመነጠል፣ ካልሆነም እርስ በእርሱ ሃሳብ በመከፋፈል ቀስ በቀስ በአማራነት የሚያቀነቅኑትን አካሎች አንድ በአንድ በማጥፋት ያለ ተቀናቃኝ አካባቢውን እንደገና ለመቆጣጠርና ከቀደመው መከራ የተረፈውን ዘራችንን ፈፅሞ ለማጥፋት የተጠነሰሰ የመጨረሻው ሴራ/Plan B/ መሆኑ ያገባኛል የሚል አካል ሁሉ እንዲያውቅልን በጥብቅ እናሳስባለን።
ይህ ሴራ ቀደም ብሎ የተገነዘበው ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን በ2004 ዓ.ም የተለያዩ መድረኮችን በመጠቀም አቋሙን ግልፅ ያደረገ ሲሆን፣ ከጉዳዩ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ብዥታዎችም በሰፊው መልስ ተሰጥቶበታል። ለበለጠ መረጃና ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ማስፈንጠሪያውን በመጫን ሙሉ ሃሳቡን ማግኝት ይቻላላ። “የአቸናፊዎች ፍትህ”
በአጭሩ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ጥያቄ በወረራ የተወሰደው መሬቱና በሃይል የተገፈፈው አማራነቱ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ማስመለስ እንጂ በወረራ ለሰፈሩት የትግራይ ተወላጆች የሚያመችና ባለ ዕርስትነት የሚያረጋግጥ “የራስ ገዝ” አስተዳደር ለመጠየቅ የሚያበቃው ምንም አይነት ምድራዊ ምክንያት የለውም። አይኖረውም። ስለሆነም ለህዝባችንና ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የምናስተላልፈው መልዕክት ቢኖር፦
1ኛ. ለወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ወገኖቻችን በሙሉ
ለአርባ አመታት ያህል ርስትህ በወረራ ተነጥቀህና በተወለድክበትና እትብትህ በተቀበረበት ቀየህ ልጅ ወልደህ እንዳታሳድግ፣ ሰርተህ እንዳትበላና፣ በድህነት እንኳ እንዳትኖር ያለበደልህ ተፈርዶብህ አንተን በማሰር፤ በማሰቃየት፣ በማፈናቀልና፣ በመግደል ታዳጊ ልጆችህ ሳይቀር የማንነት ቀውስ ውስጥ እንዲገቡና የሰነ ልቦና በሽተኞች እንዲሆኑ ለማድረግ ዓለም ሳይቀር ያወቀውና በይፋ ያወገዘው ግልፅ የዘር ማጽዳት ጥቃትን በደል በወራሪው ትህነግ/ወያኔ ተፈፅሞብሃል። ተፈፅሞብናል።
ዛሬ ሁሉም ነገር ገሃድ በወጣበት ሰአት ለደረሰብህ በደልና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሁሉ ይቅርታ ልትጠየቅ ሲገባህ፤ እንደ አዲስ “ራስ ገዝ” መጠየቅ ትችላላችሁ በሚል አሮጌ ሴራ እርስ በእርስ ለማጋጨትና ብሎም ከጎንደርና ከመላው የአማራ ህዝብ ሊነጥሉህ እየሞከሩ ይገኛሉ።። ይህን የትህነግ ንቀትና ስድብ በይፋ አጥብቀህ ልትቃወመው ይገባሃል።
2ኛ. ከትህነግ/ወያኔ ጎን ለተሰለፋችሁና ለነበራችሁ የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ተወላጆች በሙሉ
ከ40 ዓመታት በፊት በወልቃይት በጠገዴና በጠለምት ህዝብ ላይ የተጀመረው የአማራን ዘር የማጥፋት ሴራና ጥቃት ዛሬ በሁሉም መልኩ ተጋልጦና የአማራ ህዝብ በአንድነት ዘሩንና ሃገሩን ለማዳን በአንድነት የተነሳበት አዲስ ዘመን ላይ እንገኛለን።
በሌላ በኩል መላው የኢትዮጵያና የዓለም ህዝብ የትህነግን እኩይ አላማና ተራ የሌብነት ተግባር በተጨባጭ ማስረጃ ያረጋገጠና በዚህም ወራዳና ብልሹ መንግስታዊ ምግባር ምክንያት ሃገራችን ኢትዮጵያ ከገባችበት አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣት ሁሉም በይቅርታና በፍቅር ከለውጥ ሃይሉ ጋር እየተሰለፈ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል።
ስለሆነም ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንያቶች ከትህነግ ጎን በመሰለፍ የወልቃይት፣ የጠገዴንና የጠለምትን ህዝብ ጥቅሞች ለወራሪው ሃይል አሳልፋችሁ የሰጣችሁና እስከ ዛሬ ድረስ በህዝባችን ላይ የሚፈጸመውን የዘር ማፅዳት ወንጀልና ከርስቱ የማፈናቀል ግፍ አባሪና ተባባሪ በመሆን፣ አይቶ እንዳላየ በመሆን፣ ይልቁንም በህዝባችን መካከል የትህነግን የመከፋፈያ ሴራ በማሰራጨትና በማራገብ የወገናችሁን አንድነቱንና ህብረቱን ስታዳክሙ የነበራችሁ ሁሉ እስከዛሬ የበደላችሁትን ህዝብ ለመካስና በይቅርታ ወደ ወገናችሁ ለመመለስ ጊዜው የዘገየ ቢሆንም አሁንም እድሉ ጨርሶ አልተዘጋም ብሎ ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን ያምናል።
ስለዚህ ዛሬ ነገ ሳትሉ በግላጭ የበደላችሁትንና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለጠላት አሳልፋችሁ የሰጣችሁትን ህዝባችሁን በአደባባይና በይፋ ይቅርታ በመጠይቅ በሩ ሳይዘጋ ወደ ነጻነቱ ድንኳን እንድትገቡና ወገናችሁ እያደረገ ወደ ሚገኘው የህልውና ትግል በይፋ እንድትቀላቀሉ ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን ጥሪውን ያቀርባል።
3ኛ. ለጎንደር የወሎና መላው የአማራ ህዝብ
ፋሽስቱ ትህነግ ለአለፉት 40 ዓመታት የአማራን ዘር ለማጥፋት በእቅድ የተደገፈ ጥቃትና በደል አድርሷል። ይህ አኩይ ወንጀል ምንም እንኳ ሲጀምር የጎንደርን ለም መሬቶች በመውረርና በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት የሚኖሩ የአማራ ወገኖችህ በማጥቃት ቢሆንም በሂደት ግን ሁሉንም የአማራ ልጆች በደረሱበት ሁሉ በማሳደድና በማጥፋት ላይ ያተኮረ እንደነበር ያለፉት 27 የሰቆቃ ዓመታት አረጋግጠውልናል።
ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ልጆች የተባበረ ክንድ ወደ ዘላለማዊ መቃብሩ የወረደው ትህነግ፤ ዛሬም በሞት ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ በቅሬት አካሎቹና በማደጎ ልጆቹ በኩል ሴራን እየጎነጎነ እና የጥላቻ መርዙን ወደ ምድራችንና ወደ ህዝባችን እየረጨ ይገኛል። በተለይም በአሁኑ ሰአት በወልቃይትና በራያ ማህበረሰብ ውስጥ ብዥታን እንዲፈጥሩና ትግሉን እንዲያዳክሙ “ትግሬም አማራም አይደለንም” የሚሉ ቀለብ የተሰፈረላቸው ርዝራዦቹን አሰማርቶ ይገኛል።
ይሁን እንጂ ዛሬ የወልቃይትም ሆነ የራያ ህዝብ የህልውና ትግል ከተወላጁ እጅ የወጣና በመላው የአማራ ህዝብ ትክሻ ላይ የወደቀ መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት አይገባም። ስለሆነም የወልቃይት ህዝብም ሆነ የራያ ህዝብ ለትህነግ ፈርጀ ብዙ ጥቃት ሳይንበረከክ ለመላው የአማራ ህዝብ ያስረከበውን ትግል መላው የአማራ ልጅ በሙሉ ሃላፊነትና የባለቤትነት ስሜት በርትታችሁ ፍፃሜ ላይ ታደርሱት ዘንድ ማሳሰብ እንወዳለን።
ይልቁንም መላው የጎንደር የወሎና የአማራ ልጆች ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በአንድነትና በእኩልነት ጸንተን በመቆምና ፍትሃዊ የህልውና ትግላችንን ከምንግዜውም በላይ አጠናክረን በመቀጠል ትህነግና ዘረኛ አላማው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያችን ላይ ለማስወገድ በአንድነት እንድንነሳ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
4ኛ. ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ
የአልፉት 27 ዓመታት የሰቆቃ ዘመን ምን ይመስል እንደ ነበር ለኢትዮጵያ ህዝብ መንገር ማለት ለቀባሪ ማርዳት ይሆንብናል።
አንድን ታላቅ ህዝብ በዘር ከፋፍሎና በክልል በታትኖ እርስ በራስህ በጥርጣሬ እንድትተያይ፣ እንድትጨካከንና፣ ብሎም እንድትጠፋፋ የተሴረብህን የእኩዮች ሴራ ከተረዳሃው ውለህ አድረሃል ብለን እናምናለን። የዚህ በደል የመጀመርያው ገፈታ ቀማሽ ወገናችሁ የወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምት ህዝብ መሆኑና ይህም በደል ለአለፉት 38 ዓመታት ተጠናክሮ እንደቀጠለና ከኢትዮጵያ ህዝብ ፈላጭ ቆራጭነት መንበሩ የተወገደውና ትግራይ ውስጥ መሽጎ ታሪካዊ ሞቱን የሚጠባበቀው የትህነግ እኩይ ሃይል ዛሬም የወልቃይትና የራያን ንጹሃን ወገኖችህን እያፈናቀለና እየገደለ ይገኛል።
ሥለሆነም ህዝባችን ከትህነግ ፋሽስታዊ ጥቃት እራሱን ለመታደግና ህልውናውን ለማዳን በሚያደርገው ትግል ከጎኑ በመቆም ፀረ-ትህነግ ትህነግ ትግልህን አጠናክረህ እንድትቀጥል ልሳነ ግፉአን ጥሪ ያቀርባል።
5ኛ. ለኢትዮጵያ መንግስትና ለለውጥ ሃይላት በሙሉ
ድርጅታችን ልሳነ ግፉዓን በተከበሩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ መሪነትና በተከበሩ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ረዳትነት የሚመራውን የኢትዮጵያ መንግስትና በእናንተ ዙሪያ ለተሰለፈው የለውጥ ሃይል ሙሉ አክብሮትና አድናቆት አለው።
ምንም እንኳ በወልቃይት፣ በጠገዴ፣ በጠለምት፣ በራያ፣ በአላማጣ፣ በአዘቦ የአማራ ወገናችን ላይ የሚፈጸመው እስራት፣ ማፈናቀል፣ ስደትና፣ ግድያ ጋብ ያላለ ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝብ ባገኘው አንፃራዊ ተስፋና ሰላም ምክንያት ዛሬም ከጎናችሁ መቆማችንና የለውጥ ሃይሉ ግንባር ቀደም አጋር መሆናችንን ስንገልፅ በእውነተኛ ወገናዊነትና በታላቅ ኩራት ነው።
ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታና ወደ ህግ ልዕልና የሚደረገው የለውጥ እርምጃ ህዝብ ውስጥ እንዲወርድና ለዘላቂነቱም መዋቅራዊ እንዲሆን እየተወሰደ ያለውን ጥረት እናደንቃለን። ምንም እንኳ ቀስተኛ የሆነውና ጥንቃቄ የተሞላበት የለውጥ ጉዞ ቢያስደስተንም ወደ ህዝባችን የሚደርስበትና የወገናችን የዘመና ት ሰቆቃ የሚቆምበትና እንባው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚታበስበት ጊዜ መቼ እንደሚደርስ እጅግ ያሳስበናል።
ፋሽስቱና የአማራ ወንድ ልጆችን እስከ ማኮላሸት የሰየጠነው ጌታቸው አሰፋ ከስልጣን መወገድ ጀምሮ በየክልሉ ተሰግስገው የኢትዮጵያን ልጆች ደም ሲመጡና ምድሪቱን ሲኦል ሲያደርጓት ያረጁት የትህነግ መሪዎችና የጡት ልጆች ቀስ በቀስ ከየቦታው መነቀላቸው የለውጡን መሪዎች በሙሉ ልባችን እንድንደግፍና በቀጣይነት ለምታከናውኗቸው መሰረታዊ የለውጥ እርምጃዎች በቂ ግዜ እንደሚያስፈልጋችሁና በትዕግስትም እንድናግዛችሁ የግድ ይለናል።
በተለይም በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተካሄደውና መንግስታዊ ስልጣኑን ተጠቅሞ መላውን የአማራ ልጅ፣ በተለይም የወልቃይትን ልጆች በህግ አደባባይ ሲያሳድድና ሲያሰቃይ የኖረው የትህነጉ ቀኝ እጅ ወልቃይቴ ባንዳው አቶ ፀጋዬ አስማማው ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዘደንትነት ስልጣን መናሳቱ ለውጡ ጥርስ እያወጣና ተቋማዊ እየሆነ ለመምጣቱ፣ የህዝባችንም የዘምናት ችግር በትግላችን ይወገዳል የሚል ተስፋ እንድንሰንቅ አድርጎናል።
በዚህ ብሩህ ተስፋ ውስጥ ሆነን ለውጡ ፌደሬሽን ምክር ቤት መቼ እንደሚደርስና የትህነጓን ወ/ሮ ኬሪያ መቼ እንደ ሚጎበኛቸው በጉጉት እየጠበቅን ሲሆን፣ በተለይም የወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ በቀጥታ የሚቀርበው ለአፈ-ጉባኤዋ የመሆኑ ጉዳይና ሴትየዋም የትህነግ ማዕከላዊ ምክር ቤት አባል መሆናቸው ሳያንስ የሚያሳዩት አይን ያወጣ ወገንተኝነትና ኢፍትሃዊ አሰራር ከምንታገሰው በላይ ሆኖብናል።
ስለሆነም የዶ/ር አብይ መንግስትና ካቢኔን ከታላቅ አክብሮት ጋር የምንጠይቀው ፈጣን እርምጃ ቢኖር ህዝባችን በወ/ሮ ኬሪያ እብሪትና ፌዝ አዘል ምላሾች ምክንያት በመሰላቸት ብቻ ወደ ከፋ ቁጣና አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ ከመግባቱ በፊት በአስቸኳይ አፈ-ጉባኤዋን ከቦታቸው እንዲነሱና ከአማራና ከትግሬ ውጭ የሆነ ማንኛውም ገለልተኛ ብሔር ቦታውን እንዲይዘው እንዲደረግ በአክብሮት እንጠይቃለን።
6ኛ. ዛሬም እንደገና ለመላው የትግራይ ሕዝብ
ውድ ወገናችን! ሰላማዊውና ሃገር ወዳዱ ሰፊው የትግራይ ህዝብ ሆይ!
ለዘመናት እየተፈራረቁብን በአንድነት ቆመን ላስተናገድናቸው የደስታና የመከራ ጊዚያትን ወደ ኋላ መለስ ብለህ እንድታስታውስ በፍቅር አምላክ! በኢትዮጵያ አምላክ! ስም ዛሬም እንለምንሃለን። ለአያሌ ዘመናት ደምህን ከደሙ ጋር አብረህ የቀላቀልከውን መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ ቆም ብለህ አስብ! ይልቁንም ጎረቤትህ የሆነውንና በክፉም ሆነ በበጎው ሮጦ የሚደርስልህንና የምትደርስለትን የአማራ ህዝብ እንዲሁ ዛሬ ቆም ብለህ አስብ! ይልቁንም አጉራሽህን ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ራያና አዘቦን፣ አላማጣና ኮረምን አብዝተህ አስብ!
የሰው ወርቅ አያደምቅ ነውና ያንተ ያልሆነውን ርስት በሃይል መውሰዱ ለግዜ ያስደስት ይሆናል ዙሮ ዙሮ ግን ወጤቱ አያምርምና ለጥፋት እየመሩህ ያሉትን መሪዎች አስቁማቸው። የሌላውን ድርሻ በሰላም ለባለቤቱ መልሱ እንድትላቸው በጥብቅ እናሳስባል። ጦርነት ለማንኛችንም የሚበጅ አይደለም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በተደረገው ጦርነት የተገኘው ውጤት ድምሩ ዜሮ ነው። ወደ ለመዱት የጥፋት ጉዞ እየመሩን ያሉት ልጆችህ አደብ ግዙ መባል ይገባቸዋል።
ሌባና ወንጀለኛ ልጆችህ ዛሬውኑ ቅጣ! ከወገንህ ጋር ሊያዋጉህ ምሽግ ሲያስቆፍሩህና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ሲያስታጥቁህ እልል ብለህ አትቀበላቸው! እነርሱ ተራ ሰዎች ናቸውና ያልፋሉ። የማያልፈው ሃገርና ትውልድ ነውና ከሃገርህ አትነጠል! ለጥቂት ወንጀለኞች ብለህ ለመጭው ትውልድ የማያልፍ እዳ አታስቀምጥ! ይልቁንም እጃቸውን ይዘህ አሳልፈህ ለመንግስት ስጣቸው! መንግስት እንደ ወንጀላቸውና በደላቸው በህግ ይዳኛቸው!
በመጨረሻም የፌደራሉ መንግስት በግልፅ እንደሚያውቀው ትህነግ መራሹ የትግራይ ክልላዊ መንግስት በወልቃይትና አካባቢው ውስጥ የጦርነት ምሽግ እየቆፈረና ለጦርነት እየተዘጋጀ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ቀን በቀን ሰላማዊ ህዝብን በጥይት አረር ይጨፈጭፋል፣ በጀምላ ያፈናቅላል። አልፎ ተርፎ በቅማንት ተወላጅ ወገኖቻች ስም በድሽቃ የታገዘ ጦርነት በጎንደር ህዝብ ላይ ከፍቶ ይገኛል።
የትህነግ ወንጀለኛ አመራሮች ይህን ሁሉ እሳት በአማራና በትግራይ ክልል ዙሪያ የሚለኩሱት ግልፅ በሆኑ ምክንያቶች ነው።
1ኛ. በሃገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ሁለገብ ለውጥ ለማደናቀፍ በመላው ሃገሪቱ ሊያቀጣጥለው ሞክሮ በሶማሌ፣ በጋምቤላ፣ በአፋርና፣ በደቡብ ክልሎች የለኮሰው ቀውስ በመክሸፉ ምክንያት ወደ ትህነግ የመጨረሻ ምሽግ የሚደረገውን የለውጥ ጉዞ እየተፋጠነ በመምጣቱ ሲሆን፣
2ኛ. የአማራና የትግራይን ህዝብ ወደ ለየለት የእርስ በእርስ ግጭትና ትርምስ በማስገባት በትግራይ ውስጥ በሚገኙ የአማራ ተወላጆች የዘር ፍጅት ለመፈጸምና የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጵያ በመገንጠል እስከ መጨረሻው ታሪካዊ ሞቱ ድረስ በመያዦነት ለምያዝ በማለም ነው።
ስለሆነም በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኙ የአማራ ተወላጆችና በተለይም የአማራ የማንነት ጥያቄ ባነሱ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምት፣ የራያ፣ የአላማጣ፣ የአዘቦ፣ … ወዘተ ወገኖቻችን ደህንነት ከምንግዜውም በላይ ያሳስበናል።
በእነዚህ ወገኖቻችን ላይ የከፋ ችግር ከመፈጠሩ በፊትና አካባቢው ወደ ለየለት ቀውስ ውስጥ ከመግባቱ በፊት የፌደራሉ መንግስት ጣልቃ እንዲገባና የመከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ሰፍሮ የህዝብ ደህንነትና ሰላም እንዲጠብቅ እንዲደረግ ስንጠይቅ እያንዳንዷን ደቂቃ የምናሳልፈው ከላቀ ስጋትና ጭንቀት ጋር መሆኑን በመግለፅ ነው።
ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለህዝባችን!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!
ልሳነ ግፉዓን ድርጅት
ጥቅምት 27, 2011 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*